“ጦርነት የገጠምነው ርስት ፍለጋ አይደለም”-አቶ አገኘሁ ተሻገር፣የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር
ጭፍጨፋ በተፈጸመባቸው አካባቢዎች አሁንም እርሻ ውስጥ አስክሬን እየተገኘ እንደሆነ በአካል ተገኝተው ማረጋገጣቸውንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል
ርዕሰ መስተዳድሩ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍትሕ እንዲሰጠን እፈልጋለን”ም ብለዋል
ጥቃት ሲፈጸም የአማራ ሕዝብ ወጊያ የገጠመው መሬት ፍለጋ ሳይሆን ሕዝቡ የተቀማውን ማንነት ለማስመለስ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር አስታወቁ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በሕግ ማስከበር ዘመቻው የተሳተፉ የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ሠራተኞችን ዕውቅና ለመስጠት በተዘጋጀው መድረክ ላይ “አንዳንድ አካላት ጦርነት የገጠምነው ርስት ፍለጋ አድርገው ማሰባቸው ትክክል አይደለም” ብለዋል፡፡
ሕግ በማስከበር ዘመቻው ላይ “የአማራ ሕዝብ የተሳተፈው መሬት ፈልጎ አይደለም”ያሉት አቶ አገኘሁ ጦርነቱ የፍትህና የመገፋት እንደነበር አንስተዋል፡፡ የህወሃት ቡድን ጥቃት እንደሚፈጽም እንደሚያውቁ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ በየትኛው በኩል እንደሆነ ግን ማወቅ አይቻልም ነበር ብለዋል፡፡
ይሁንና ህወሃት በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በፈጸመበት ዕለት በአማራ ሕዝብም ላይ ቀጥተኛ ጥቃት በመሰንዘሩ ይህንን የመከላከል ሥራ መከናወኑን ነው የተናገሩት፡፡
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ሌሊት ላይ ፋሻ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጥቃት ሲፈጸም ቦታው ላይ የነበረው የአርማጭሆ ሚሊሻ እንደነበር ገልጸው ወዲያው ከተማ ንጉስን መቆጣጠር ችሏል ብለዋል፡፡
“ህወሃት የአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ ጥሼ ጠዋት ጠገዴን ተቆጣጥሬ፤ ምሳ ጎንደር፣ እራት ደግሞ ባህር ዳር አደርጋለሁ” የሚል ዕቅድ ይዞ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ይህ ህወሃት የሰራው የመጀመሪያ ስህተት እንደነበር አንስተው “ጦርነቱ የፍትህ፣ የግፉአን እንጅ የርስት ፍለጋ” እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
“ህወሃት መከላከያ ላይ የወሰደው የማይገባ ሙከራ ዋጋ አስከፍሎታል” ያሉት አቶ አገኘሁ “አሁን በወያኔ መቃበር ላይ ሆነን ነው የምናወራው” ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ሕዝቡ ከአላስፈላጊ የድል መስከር መውጣት እንዳለበትና ሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ እንደዚሁም በጦርነቱ የተጎዱትን የመደገፍ ሥራ ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት አንስተዋል፡፡
በጦርነቱ የአማራ ክልል 2 ሺ 400 ተሽከርካሪ መላኩን ገልጸው ሕግ የማስከበር ሥራው በአግባቡ እንዲከናወን ክልሉ አስፈላጊውን ሁሉ አድርጓል እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ጀግንነት እንደተጠበቀ ሆኖ “መጀመሪያ የተለበለበው የአማራ ሕዝብ ነው”ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ አንዳንዶች ይህንን ድል አኮስሰው ሊያዩት እንደሚፈልጉ እንዲሁም ያልተገባ ሚዛን ሊሰጡት እንደሚፈልጉም ነው የተናገሩት፡፡
የአማራ ክልል የጸጥታ አካላት የተዋጋው ለፍትሕ መሆኑን ገልጸው ይህንን ተከትሎ ድል ከተገኘ በኋላ አንዳንድ አካላት የአማራ ልዩ ኃይልንና ሚሊሻን ክብር ዝቅ የማድረግ አዝማሚያዎች እንዳሉ ገልጸው ይህንን ክልሉ እንደማይቀበል አስታውዋል፡፡
ሁሉንም በሚዛኑ ማየት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ላለፉት ዓመታት በጋራም በተናጠልም ትግል ሲደረግ እንደነበር አንስተው ይህንን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አዳምጠው ፍትሕ እንዲሰጡን እፈልጋለን ብለዋል፡፡
የሕዝብ ጥያቄ በሕግ እንዲመለስ እንደሚፈልጉ የገለጹት አቶ አገኘሁነማይካድራ ላይ የተጨፈጨፉት ሥራ ፍለጋ የሄዱ የአማራ ወጣቶች ናቸው ብለዋል፡፡ ይህንን ጭፍጨፋና ግፍ ዝቅ አድርጎ ሊመለከት የሚፈልግ ሀይል ካለ ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸው አሁንም እርሻ ውስጥ አስክሬን እየተገኘ መሆኑን በቦታው ተገኝተው ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ላይ ለተሳተፉ 9 ፖሊሶች እና 31 ጋዜጠኞች ለእያንዳንዳቸው የ10 ሺ ብር ሽልማት እንደሚያበረክቱ ቃል ገብተዋል፡፡