“በሰራዊቱ ውስጥ አድሎ እንዲኖር ያደረገው ጄኔራል ሳሞራ ነው አልልም” ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ
“በሰራዊቱ ውስጥ አድሎ እንዲኖር ያደረገው ጄኔራል ሳሞራ ነው አልልም” ሲሉም ገልጸዋል
ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ “በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ የተደረገው የማሻሻያ ስራ (ሪፎርም) ከጉድ አድኖናል” ብለዋል
የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሀገራዊ ከመሆን ይልቅ በጎጥ የሚያስብ እንዲሆን ሲደረግ እንደነበር የጦር ኃሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ተናግረዋል፡፡
ኤታማዦር ሹሙ ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ ጋር ባደረጉት ቆይታ ፣ ሀገራዊ ሰራዊት እንዳይገነባ የሚያደርጉ አሰራሮች ነበሩ ብለዋል፡፡
“አንዳንዱ ምንም ሳይሰራ ዕውቅና የሚሰጥበት፣ አንዳንዱ ደግሞ ብዙ ሰርቶ የማይበረታታበት አሰራር ነበር” የሚሉት ኤታማዦር ሹሙ ይሁንና የመከላከያ ሰራዊት ተቋም ስለሆነ “ሁሉንም መጥፎ ነገር ተሸክሞ” ግዳጁን ሲወጣ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
“እነዚህ ሁሉ ችግሮች እንዲፈጠሩ ያደረጉት የሰራዊቱ መሪዎች አይደሉም” ያሉም ሲሆን “እንደዚህ ያደረገው ጄኔራል ሳሞራ ነው ብዬ አልልም” ብለዋል፡፡
“ጄኔራል ሳሞራን ራሱ የሚመራው መንግስትና ፓርቲ አለው” የሚሉት ጀነራሉ “በተሰጠው አቅጣጫ ነው የሚሄደው ነው” ያሉት፡፡ ይሁንና “እሱ ይህንን ምን ያህል ይቃወም ነበር የሚለውን አላውቅም ፤ ነገር ግን አሰራሩ ትክክል እንዳልነበረ ልቦናው የሚነግረው ይመስለኛል” ብለዋል፡፡
ኢታማዦር ሹሙ “ሌሎቹ ደስ ብሏቸው” ይሰሩ እንደነበር ገልጸው የዚህ ደግሞ ምክንያቱ “አብዛኛው ከአንድ አካባቢ የመጣ” መሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የሰራዊቱ አመራሮች ከፍ ወዳለ ኃላፊነት ሲመጡ “ይህ ሰው አድጎ፤ አድጎ እኛጋ ደረሰ” ተብሎ በግምገማና በሌላ መንገድ እንዲወጣ እንደሚደረግ አንስተዋል፡፡
ይህ ሁሉ ሲደረግ አንድ ቀን የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ በማሰብ ፤ “እንቻለው እስኪ ለማነው የምንለቀው ፤ አንድ ቀን ብርሃን ይበራል እያለ ሰው ቆይቷል” ብለዋል፡፡
“በነበረው አሰራር መፍረስ የነበረበት ሰራዊት ነበር፤ ደግሞም ፈርሷል እኮ፤ አዲስ ወታደር መጥቶ ወደ ሰራዊቱ ገብቶ ሰባት ዓመት ካገለገለ በኋላ ፣ የ7 ዓመት ኮንትራት የሚባል አለ ፣ ኮንትራቱ ሲደርስ በብዙ ሺዎች ይወጡ ነበር፤ ሕጋዊ ቢሆንም ይህ የሚያመለክተው እዛ ያለውን አድሎ በማየታቸው ነው መቆየት የማይፈልጉት” ሲሉ ነው ለኦቢኤን የተናገሩት፡፡
አሁን ግን ፣ ከሰራዊቱ ይለቅ የነበረ ሰው፣ “አልሄድም እቀጥላለሁ” እያለ መሆኑን ገልጸው አሁን ላይ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ አድሎ እና አንዱን መጥቀምና ሌላውን መጉዳት የሚባል አሰራር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡
“በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ የተደረገው የማሻሻያ ስራ (ሪፎርም) ከጉድ አድኖናል” የሚሉት ጄኔራል ብርሃኑ ሪፎርሙ የሰራዊቱን ኑሮ ለማስተካከል እና ደስተኛ እንዲሆኑ ለማድረግ አግዟል ብለዋል፡፡
መንግስት ሰራዊቱ አደጋ ላይ እንዳለ ቀድሞ አውቆ ስለነበር ኑሮውን ለማስተካከል ጥረት ማድረጉን አንስተው “ድሮ ይናቅ የነበረ አመራር አሁን ጥበብ ያለው እና ጀግና” እንደሆነ መታየቱን ገልጸዋል፡፡
“የሕወሓት አመራሮች አንድን ብሔር ጀግና ሌላውን ደግሞ ፈሪ” አድርገው በመሳል የተሳሳተ አመለካከት ፈጥረው እንደነበር ያነሱት ጄኔራል ብርሃኑ ፣ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ያለው ሪፎርም ገና ያላለቀና ብዙ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን መታጠቅ እንደሚቀር ገልጸዋል፡፡
“ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሪፎርሙ እንዲመጣ ያደረጉት ዓለምንም ኢትዮጵያንም በሚገባ የሚውቁና የሚረዱ በመሆናቸው” እንደሆነ የተናገሩ ሲሆን ጄኔራሉ የሰራዊቱን ኑሮ የማሻሻሉ እና በስልጠና የማብቃት ሥራዎች የሚያልቁ ሳይሆን ሂደቶች ናቸው ብለዋል፡፡