ከበፊቱ በባሰ ሁኔታ በመጠለያ ካምፕ ውስጥ እየኖርን እንገኛለን- ወደ ኦሮሚያ ክልል የተመለሱ ተፈናቃዮች
በደህንነት ስጋት ምክንያት የምንቀሳቀሰው በሚሊሻ ታጅበን ነው ሲሉ ወደ ኦሮሚያ ክልል የተመለሱ ተፈናቃዮች ተናገሩ
ተፈናቃዮቹ በጫና መመለሳቸውን እና በባለስለጣናት የተገባላቸው ቃል አለመተግበሩን ገለጸዋል
ከአማራ ክልል ወደ ኦሮሚያ ክልል የተመለሱ ተፈናቃዮች በባለስልጣናት የተገባላቸው ቃል አለመፈጸሙን እና ከበፊቱ በባሰ ሁኔታ በመጠለያ ካምፕ ውስጥ ኑሯቸውን እየገፉ እንደሚገኙ ተናገሩ።
ባለፉት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች ውስጥ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች መፈጸማቸውን በርካታ የመብት ተቋማት ሪፖርት ማድረጋቸው ይታወሳል።
የአማራ ተወላጆች ጥቃቱን ሸሽተው የተሻለ የደህንነት ዋስትና እናገኛለን ወደሚሉት አማራ ክልል ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ሲገቡ ቆይተዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል አሁን ላይ ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ እና በአማራ ክልል የተጠለሉ ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ ቦታቸው የመመለስ ስራ ጀምሯል።
አልዐይን አማርኛ ከአንድ ወር በፊት የተጀመረው ይህ ተፈናቃዮችን የመመለስ ስራ ምን እንደሚመስል ወደ ቀድሞ መኖሪያ ቤታቸው ተመልሰዋል የተባሉ ተፈናቃዮችን አነጋገሯል፡፡
ለደህንነታቸው በመስጋት ስማችን አይጠቀስ ያሉ እና ከ15 ቀናት በፊት ከደብረብርሃን መጠለያ ጣቢያ ወደ ወለጋ ዞኖች የተመለሱ ግለሰብ "የኦሮሚያ ክልል መንግስት አመራሮች መጠለያ ካምፓችን ድረስ መጥተው አካባቢያችሁ ሰላም ሆኗል እንመልሳችሁ ሲሉን እሺ ብለን ተመለስን" ሲሉ ተናግረዋል።
መንግስት ከበፊቱ መንደራችን ከመመለስ ይልቅ መጠለያ ካምፕ ሰርቶ ነው ያስቀመጠን ያሉን እኝህ አስተያየት ሰጪ ኑሯችንን በመጠለያ ለመምራትስ የነበርንበት ደብረብርሃን ይሻለን ነበር ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡
በመጠለያ ካምፕ ውስጥ ከበፊቱ ኑሯችን በባሰ ሁኔታ እየኖርን ነው ያሉት አስተያየት ሰጪው ምግብ እና ውሃ ችግር ባይኖርም የሰላሙ ሁኔታ ግን አስጊ ነው ብለዋል፡፡
ደብረብርሃን መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ከቆያችሁ እና ወደ ኦሮሚያ አንመለስም ካላችሁ መሬታችሁን እንነጥቃችኋለን ተብለን ነው የመጣነው ያሉን ደግሞ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ናቸው፡፡
ባለስልጣናት ወደ ኦሮሚያ ክልል አስፈራርተውን ከመሷቸው በኋላ አስተማማኝ ሰላም ከሌለበት ቦታ ላይ እንዳስቀመጧቸው የሚናገሩት እኝህ አስተያየት ሰጪ “የሚጠጣ ውሃ የምንቀዳው በሚሊሻዎች እየተጠበቅን ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ከምስራቅ ወለጋ ዞን ዋዩ ጡቃ ወረዳ ባለ ትምህርተ ቤት ውስጠ በተሰራ መጠለያ ካምፕ ውስጥ ከገባ ሁለት ሳምንት እንደሆነው የነገረን ሌላኛው ተመላሽ ተፈናቃይ በበኩሉ “የአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት በገቡልን ቃል መሰረት ህጻን ልጄን ይዜ ከ500 ሰዎች ጋር ተመልሻለሁ፣ ህይወታችን እንደጓጓነው አይደልም” ብሏል፡፡
በሚሊሻ እየተጠበቁ መሆኑን የሚናገረው ይህ ተመላሽ ተፈናቃይ ሩዝ በነፍስ ወከፍ ሰባት ኪሎ፣ በቆሎ ሰባት ኪሎ የሰጡን ቢሆንም የሚጠጣ ውሃ ችግር እንዳለም አክሏል፡፡
ለምንድን ነው ወደ ቀድሞ መንደራችን እማንሄደው? ብለን ስንጠይቅ “መንደራችሁ ላይ አሁንም ኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች አሉ ከዚህ እንዳትንቀሳቀሱ ይሉናል” ብሎናል፡፡
በምስራቅ ወለጋ ስር ባለችው ሌቃ ዱለቻ ወረዳ ከአንድ ወር በፊት እንደተመለሱ የነገረን ሌላኛው ተመላሽ ተፈናቃይ አካባቢው አሁንም ለመንቀሳቀስ፣ ለማረስ እንደማይቻል ፣ሸኔ አሁንም ከበፊቱ የበለጠ ተጠናክሮ እንጂ በመንግስት የጸጥታ ሀይል እርምጃ እንዳልተወሰደበት ጠቅሷል፡፡
ይህ ሁሉ የጸጥታ ችግር ባለበት እና ከህብረተቡ ጋር እርቅ ሳይፈጸም ከቀድሞ ቤታችሁ ኑሩ እንደተባሉ የተናገረው ይህ አስተያየት ሰጪ ከሰላም ችግር ባለፈ ወፍጮ፣ መብራት እና ውሃ እንደሌለም ነግሮናል፡፡
በዚህ ምክንያት ወደ አማራ ክልል እንመለሳለን ስንል ከቀበሌያችን ካምፕ ሰርተው ኑሩ ብለውን እየኖርን ነው ሲልም አክሏል ይህ አስተያየት ሰጪ፡፡
“ከቀድሞ መኖሪያችን ውጡ ተብለን ነበር የወጣነው አሁን ደግሞ ኑ እንፈልጋችኋለን ሲሉን ደስ ብሎን ብንመጣም የተሰራ ስራ የለም ሸኔ ብሶበታል እንጂ አልተመታም” ሲል አክሏል፡፡
“አማራ ክልል የነበርነውን ተፈናቃይ እያመጡን ያለው ለፖለቲካቸው ሲሉ ነው እንጂ እኛን ለመመለስ እና ለዜጋ አስበው አይደለም ፣ማዳበሪያ፣ ዘር፣ እርሻ፣ ማረሻ ማቋቋሚያ እንደሚሰጡን ቃል ገብተውልን ነበር፣ ስንጠይቃቸው ግን ይስቁብናል፣ እርሻችንን ማረስ እሚያስችል ሁኔታ የለም” ብሏል፡
የኦሮሚያ ክልል መንግስት ተመላሽ ተፈናቃዮች ባነሷቸውን ጥያቄዎች እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጥን ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም፡፡
መንግስት በአሮሚያ ክልል ለሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች በሽብር የተፈረጀውን 'ኦነግ ሸኔ' በተደጋጋሚ ተጠያቂ ያደርጋል።
በመንግስት እና በ'ኦነግ ሸኔ' መካከል ከወራት በፊት በታንዛኒያ የተደረገው ድርድር ያለውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል።