ሀገራቱ ቻድ፣ ኢትዮጵያና ዛምቢያ ዓለም አቀፍ ተቋማት ለአፍሪካ የብድር ስረዛና የመክፈያ ጊዜን እንዲያራዝሙ ለጠየቁት ጥያቄ ምላሽ ጠይቀዋል
የበለጸጉ አገራት ለአፍሪካ 30 ቢሊዮን ዶላር ፈሰስ እንዲያደርጉ የአፍሪካ አገራት አሳስበዋል።
የናይጀሪያ፣ ጋና፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ኮቲዲቯር የገንዘብ ሚኒስትሮች ለዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) በጻፉት ደብዳቤ የበለጸጉ አገራት 30 ቢሊየን ዶላር ለአፍሪካ እንዲመድቡ ጠይቀዋል።
አገራቱ በደብዳቤያቸው እንደጠየቁት አፍሪካ በኮሮና ቫይረስ ከደረሰባት ጉዳት እንድታገግም የገንዘብ ድጋፍ ያስፈልጋታል ብለዋል።
ገንዘቡ አፍሪካዊያን ከኮሮና ቫይረስ በተጨማሪ በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ለደረሰባት ጉዳት መካሻ እንደሚውልም አገራቱ በደብዳቤያቸው ማከላቸውን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ) 650 ቢሊየን ዶላር በመጠባበቂያነት ለመመደብ በሂደት ላይ ሲሆን፤ የፊታችን ነሀሴ ድረስ ሂደቱ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።
እነዚህ የአራት የአፍሪካ አገራት ሚኒስተሮች በደብዳቤው ላይ እንደጠቆሙት አይ.ኤም.ኤፍ ከዚህ በፊት በገባው ቃል መሰረት ከአዲሱ መጠባበቂያ አቅዱ ላይ ለአፍሪካ ሊሰጥ ስላሰበው ብድር እና በጀት ምደባ ግልጽ እንዲያደርግም አሳስበዋል።
ቻድ፣ ኢትዮጵያ እና ዛምቢያ የበለጸጉ አገራት እና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ለአፍሪካ የብድር ስረዛ እንዲያደርጉ እና የመክፈያ ጊዜን እንዲያራዝሙ በሚል የጠየቁት ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጠውም ጠይቀዋል።
አይኤምኤፍ የቀረጸው የመጠባበቂያ በጀት ማስተካከያ የበለጸጉ አገራትን የበለጸ ጥቅም የሚሰጥ ነው በሚል ሀሳብ በመቅረብ ላይ ሲሆን ድርጅቱ ሊመድበው ይችላል ከተባለው በጀት ውስጥ 7 በመቶው ብቻ ወይም 42 ቢሊዮን ዶላሩ ብቻ ለ44 የአፍሪካ አገራት ሊደርስ የችላል ተብሏል።
የቡድን 20 አገራት የገንዘብ ሀላፊዎች በጣልያን ቬንስ ከተማ በመወያየት ላይ ሲሆኑ አይኤምኤፍ ለማሰባሰብ ካሰበው 650 ቢሊዮን ዶላሩ ምን ያህል እና በምን መንገድ ለድሃ አገራት ይድረስ በሚለው አጀንዳ ላይ እየተወያየ ይገኛል።
የምዕራብ አፍሪካ የገንዘብ ሚኒሰተሮች ለአይኤምኤፍ በጻፉት ደብዳቤ የቡድን 20 አባል አገራት ቢያንስ 30 ቢሊዮን ዶላር ለአፍሪካ እንዲያበድሩ ጠይቀዋል።
ይህ ብድር ለአፍሪካ ከተፈቀደ የአህጉሪቱን ዘላቂ ኢንቨስትመንት እንደሚያነቃቃም ተገልጿል።
በአፍሪካ በተጠናቀቀው ሰኔ ወር ወስጥ ብቻ 290 ሚሊዮን ክትባት እጥረት ማጋጠሙ የተገለጸ ሲሆን በቀጣዮቹ ወራት ውስጥ 1 ቢሊዮን የኮሮና ቫይረስ ከትባት ያስፈልጋልም ተብሏል።