ራይድ ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ ከተሞች አገልግሎት መስጠት ሊጀምር መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ገለጹ
ከ 42 ሺ በላይ አሽከርካሪዎች በራይድ ውስጥ እየሰሩ ነው ብለዋል ዋና ስራ አስፈጻሚዋ
ራይድ ከተጀመረ በኋላ 50 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ ተሽከርካሪዎች ወደ ስራ መግባታቸውን ኩባንያው ገልጿል
የሀይብሪድ ዲዛይንስ (ራይድ ) ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ የኢትዮጵያ ከተሞች አገልግሎት መስጠት ሊጀምር መሆኑን ገለጸ፡፡
የሃይብሪድ ዲዛይን (ራይድ) መስራችና ሥራ አስፈጻሚ ሳምራዊት ፍቅሩ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኩባንያቸው፤ ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ ከተሞች ላይ አገልግሎት ለመጀመር መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
አገልግሎቱን ከአዲስ አበባ ውጭ ለመጀመር ጥናት መካሄዱን ገልጸው በአንድ ጊዜ በአምስት ከተሞች ላይ ይጀመራል ብለዋል፡፡ ስራውን ከአዲስ አበባ ውጭ የመጀመር ሃሳብ የቆመው በሀገሪቱ ባለው አሁናዊ ምክንያት መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ከአዲስ አበባ ውጭ አገልግሎቱን ለመጀመር ተቋሙ ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
አል ዐይን አማርኛ ራይድ በየትኞቹ ከተሞች አገልግሎት እንደሚጀምር ጥያቄ ያቀረበላቸው ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አሁን ላይ አምስቱን ከተሞች ከመናገር ተቆጥበው፤ በእርግጠኝነት ግን ስራው ይጀመራል ብለዋል፡፡
ራይድ ሁኔታዎቹ ሲጠናቀቁ በማንኛውም ሰዓት አገልግሎቱን ለመጀመር መዘጋጀቱንም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ለአል ዐይን አማርኛ አስታውቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኩባንያዎች የተወሰነ ከሰሩ በኋላ እየተዘጉ እየተመለከትን “ቢሆንም ራይድ ግን ሳምራዊት ኖረችም አልኖረችም ወደፊት የሚቀጥል ድርጅት ነው” ብለዋል፡፡
የራይድ አሽከርካሪዎች አደጋ የሚደርስባቸው ከስርዓት (ሲስተም) ውጭ ሲሰሩ እንደሆነ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገልጸዋል፡፡ የተዘረጋው ስርዓት ለደህንነት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቅሰው ፤ ቴክኖሎጂው ጥቅም ላይ ከዋለ” ማ የት ሄደ ፤ አደጋው የደረሰው የት ደርሰው ነው`` የሚለው ስለሚታወቅ አሽከርካሪዎች ከስርዓት ውጭ መስራት የለባቸውም ብለዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚ በአሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ከፖሊስ ጋር እየተሰራ እንደሆነ ያነሱ ሲሆን የአሽከርካሪዎችን ደህንነት 24 ሰዓት የሚከታተሉ ባልደረቦች እንዳሉ አንስተዋል፡፡
በትራንስፖርት ዘርፍ ራይድን ተከትሎ ሌሎችም ወደ ትራንስፖርት ዘርፍ መግባታቸውን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ በዚህም ኩባንያቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በቡና እና በአትሌቶቿ የምትታወቀው ኢትዮጵያ በቴክሎጂም ዘርፍም እንድትታወቅ ለመስራት መዘጋጀታቸውን የገለጹት ሳምራዊት ፍቅሩ፤ የኢትዮጵያ ትራንስፖርት በቴክሎጂ እንዲቀላጠፍና ይህም ወደ ምስራቅ አፍሪካ ብሎም ወደ አውሮፓም እንዲስፋፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡
እንደ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ገለጻ ራይድ ከሰባት አመት በፊት የተመሰተረው ራይድ አሁን ላይ ከ42ሺ በላይ ተሽከርካሪዎች ስራ ገብተዋል፡፡ 50 ቢሊዮን ግምት ያላቸው ተሽከርካዎች ስራ መሆናውን የገለጹት ስራ አስፈጻሚዋ ራይድ መንግስት ታክስ እንዲያገኝና የተሽካርካሪዎቹ ባለቤቶች ደግሞ የእለት ገቢ እያገኙ ነው ብለዋል፡፡