“በመልሶ ማደራጀቱ ሂደት ምንም አይነት የሚበተን ኃይል እንደሌለ ሊታወቅ ይገባል”- የአማራ ክልል
የአማራ ክልል ልዩ ኃይሎች በየካምፓቸው ወይም በተመደቡበት የስራ ቦታ ተመልሰው ተረጋግተው እንዲጠብቁ ጥሪ ተላልፏል
የክልሉን ህዝብ “መብት እና ጥቅም የሚጋፋ የትኛውንም አይነት ውሳኔ ተግባራዊ እንደማያደርግም” አስታውቋል
የአማራ ክልል መንግስት ልዩ ኃይሎችን መልሶ በማደራጀት ሂደት ምንም አይነት የሚበተን ኃይል የሌለ መሆኑን ገንዛቤ ውስጥ ሊገባ ይገባል ሲል አሳሰበ።
ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፤ ከሰሞኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ ዋና አጀንዳ ከሆኑት ብሄራዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነውና በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የልዩ ኃይል አደረጃጀቶችን መልሶ የማደራጀት ተግባር ዋነኛ እና ብቸኛ ምክንያትም ዓላማው የኢትዮጵያን ሕልውናን የበለጠ የማበርታት የጋራ ግብን ያነገበ ነው ብሏል።
“የልዩ ኃይል ፖሊስ አደረጃጀቶችን መልሶ የማደረጃት ወይም የሪፎርም ስራ በሁሉም የፌዴራልና ክልላዊ መንግስታት መሪዎች የጋራ ስምምነት ጠንካራ የፀጥታ መዋቅር እንዲኖረን ታስቦ የተለያዩ ማራጮች ለልዩ ኃይል አባላቶቻችን ታሪካዊ ተግባር ነው” ብሏል።
- የክልል ልዩ ኃይሎች ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ እንቅስቃሴ ማካሄድ መጀመሩን መንግስት አስታወቀ
- ልዩ ኃይል እንዲፈርስ መወሰኑን ተከትሎ በአማራ ክልል ተቃውሞ ተቀሰቀሰ
ተግባሩም ለሁሉም ክልል የልዩ ኃይል አደረጃጀቶች የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌድራልና የክልል መደበኛ ፖሊስ፣ የፌዴራልና የክልል የማረሚያ ቤቶችን ፖሊስ አባል እንዲሆኑ አማራጮች ያቀረበ ብሔራዊ ተግባር መሆኑንም ክልሉ በመግለጫው አስታውቋ።
እውነታዉ ይሄ ሆኖ ሳለ አንዳንድ አካላት የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን አየር ላይ እንዲበተን እየተደረገ ነው የሚል ከእውነት የራቀ መረጃዎችን በማሰራጨት የልዩ ኃይሉን አንድነት የሚረብሽ፣ ባልተገባ መንገድ ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርጉ እንቅስቃሴ ላይ ተጠምደው ይገኛሉ።
“ድርጊቱም ህዝባችንና የልዩ ኃይል አባሎቻችንን በተጨባጭ እየረበሸ ይገኛል” ብሏል የክልሉ መንግስት በመግለጫው።
“የመልሶ ማደራጀት ስራ የሚከውነው የልዩ ኃይሉን የሰው ኃይል ለበለጠ ፋይዳ ላለው ተልዕኮ መልሶ የማደራጀትና ብቁ የማድረግ ሀገራዊና ክልላዊ ፋይዳ የማዘጋጀት ተግባር እንጅ በመልሶ ማደራጀቱ ሂደት ምንም አይነት የሚበተንም ኃይል የሌለ መሆኑን ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል” ብሏል ።
“የክልሉ ህዝብም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የክልሉን ሕዝብ መብትና ጥቅም የሚጋፋ የትኛውንም አይነት ውሳኔ ተግባራዊ እንደማያደርግ ሕዝባችን ሊያውቀው ይገባል” ብሏል መግለጫው።
የተጀመረውን ልዩ ኃይሉን መልሶ የማደራጀት ስራ በውይይትና እና በመተማመን የሚፈፀም በመሆኑ የልዩ ኃል አባላት “በየካምፓችሁ ወይም በየተመደባችሁበት የስራ ቦታ በመመለሰ ተረጋግታችሁ በትግስት እንድትጠብቁ” ሲል የክልሉ መንግስት ጥሪ አቅርቧል።