የሴቶች ንጽህን መጠበቂያ ምርቶች ከግብር ነጻ እንዲሆኑ በድጋሚ ተጠየቀ
መንግስት በሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ላይ የጣለውን ቀረጥ እንዲያነሳ ያለመ ውይይት ተደርጓል
በኢትዮጵያ ታዳጊ ሴቶች በወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ እጥረት ምክንያት በየወሩ ሶስት ቀናት ከትምህርት ገበታቸው ይቀራሉ ተብሏል
የሴቶች ንጽህን መጠበቂያ ምርቶች ከግብር ነጻ እንዲሆኑ በድጋሚ ተጠየቀ፡፡
መንግስት በሴቶች የንጽህና መጠበቂያ አልባሳት ላይ የጣለውን ቀረጥ እንዲያነሳ ያለመ ውይይት በአዲስ አበባ ተደርጓል፡፡
በውይይቱ የተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት መሪዎችን ጨምሮ በሴቶች መብቶች መጠበቅ ዙሪያ የሚሰሩ የሚሰሩ ተቋማት እና ግለሰቦች ተሳትፈዋል፡፡
ለሴቶች መብት መከበር ከሚሰሩ ተቋማት መካከል ጀግኒት የተሰኘው ሀገር በቀል ተቋም መስራች የሆነችው ድምጻዊ ጸደንያ ገ/ማርቆስ “መንግስት ተፈጥሮን ሊቀርጥ አይገባም” ብላለች፡፡
ሴቶች በወር አበባ የሚጎዱት ፈልገው አይደለም የምትለው ድምጻዊ ጸደንያ ተፈጥሯዊ በሆኑ ችግሮች ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች እየተጎዱ ነው ስትል አክላለች፡፡
የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ወይም ጥሬ እቃዎች ከቀረጥ ነጻ ሆነው በተመጣጣኝ ዋጋ ለሁሉም ሴቶች ተደራሽ ሊሆኑ ይገባል ይህም መብታችን በመሆኑ መንግስት ይስማን ስትልም ጥሪ አቅርባለች ታዋቂዋ ድምጻዊ፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የሴቶች ህጻናት እና ወጣቶች ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ብርሃኑ አረጋ በበኩላቸው የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያን ጨምሮ ሌሎች የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ምርቶች አለመኖር በተለይም ታዳጊ ሴቶችን እየጎዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ 30 ሚሊዮን ታዳጊዎች በትምህርት ቤት ውስጥ መኖራቸውን የተናገሩት አቶ ብርሃኑ ከዚህ ውስጥ የሴቶች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው በንጽህና መጠበቂያ እጥረት ምክንያት አንድ ሴት ተማሪ በአማካኝ በወር ሶስት ቀናትን ከትምህርት ገበታ ውጪ እንደምትሆን ጠቅሰዋል፡፡
በዓመት ደግሞ አንድ የወር አበባ ማየት የጀመረች ሴት ተማሪ አቅርቦቱ ባለመኖሩ ምክንያት የ30 ሰዓታት ትምህርት እንደሚያመልጣትና ይህም ሴቶችን ለሌሎች ውስብስብ ችግሮች እያጋለጣቸው መሆኑን አክለዋል፡፡
በመሆኑም መንግስት የሴት ንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን ከቀረጥ ነጻ እንዲሆኑ የገባውን ቃል እንዲተገብር ትምህርት ሚኒስቴር ግፊት በማድረግ ላይ መሆኑንም አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ አሁን ላይ ለአንድ ጊዜ አገልግሎት የሚውሉ የወር አበባ የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ከ50 ብር እስከ 100 ብር ድረስ በመሸጥ ላይ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡
በዋጋ መናር ምክንያትም 72 በመቶ የሚሆኑት በገጠር የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖሩ ወጣት ሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን እንዳማያገኙ የኢትዮጵያ የስነ-ህዝብ፣ ጤናና አካባቢ ጥበቃ ጥምረት የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ያጠናው ጥናት ያሳያል።