የዓለም ጤና ድርጅት "ሞንኪ ፖክስ" የሚለውን መጠሪያ ሊቀይር ነው
ዶ/ር ቴድሮስ ለቀጣይ ሳምንት የድርጅቱን የአደጋ ጊዜ ኮሚቴ ለድንገተኛ ስብሰባ ጠርተዋል
ስያሜው መገለልን ሊያስቀር በሚችል መልኩ ይቀየራል ተብሏል
የዓለም ጤና ድርጅት "ሞንኪ ፖክስ" የሚለውን መጠሪያ ሊቀይር ነው፡፡
ስያሜው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በብዙ ሃገራት እየተዛመተ የሚገኘውን የፈንጣጣ በሽታ ዝርያ ለመለየት የተሰጠ ነበር፡፡
ሆኖም በሽታው ከተወሰነ አህጉር እና ሃገራት ህዝቦች ጋር እየተያያዘ መገለልና መድሎ አምጥቷል፡፡በመሆኑም እየተያያዘ የሚሰጠውንና የሚለጠፈውን ስም ለማስቀረት በሚያስችል መልኩ ስያሜውን እንደሚቀይር ነው የዓለም ጤና ድርጅት ያስታወቀው፡፡
የስያሜ ለውጡ በቅርቡ እንደሚደረግም የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ የስያሜ ለውጡን የሚያደርገው 30 ገደማ ሳይንቲስቶች በደብዳቤ ባቀረቡት ጥያቀ መሰረት ነው፡፡
ሳይንቲስቶች ምዕራብ ማዕከላዊ በሚል ከኮንጎ ተፋሰሶች ጋር መያያዙን ሊያስቀር በሚችል መልኩ ስያሜው እንዲቀየርም ጠይቀዋል፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ ትናንት በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ̒ ̒ ስያሜውን ለመቀየር በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ባለሙዎች ጋር እየሰራን ነው̓ ̓ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ በሽታው እየተዛመተ መሆኑን ተከትሎ በወረርሽኝ ደረጃ ሊፈረጅ የሚችልበት አግባብ ካለ ለመወያየት የድርጅቱን የድንገተኛ አደጋዎች ኮሚቴ ለቀጣይ ሳምንት ሃሙስ ለአስቸኳይ ስብሰባ መጥራታቸውንም ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ ከአሁን ቀደም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከቻይና የመጣ እንደሆነ ተደርጎ በሚነዙ አሉባልታዎች ምክንያት ሊደርሱ የሚችሉ መገለሎችንና ጥቃቶችን ለመከላከል በሚል የቫይረሱን ስያሜ ወደ ኮቪድ-19 መቀየሩ ይታወሳል፡፡
"ሞንኪ ፖክስ" በ1950ዎቹ በተለያየ ምድብ ተለይተው በዝንጀሮዎች ላይ ሲደረጉ በነበሩ ምርምሮች ነው መኖሩ የታወቀው፡፡ በቫይረሱ የተያዘ የመጀመሪያው ሰው የተገኘውም በ1970ዎቹ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ነው፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ እስካሁን ከ2 ሺ በላይ ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን የድርጅቱ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡