ፖለቲካ
የደቡብ ምስራቅ እስያ ዓመታዊ የጸጥታ ስብሰባ በፉክክር የተሞላ ነው ተባለ
የቻይና፣ የአሜሪካ እና የሩሲያ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች የጸጥታ ስብሰባውን ይካፈላሉ ተብሏል
ጉባኤው ክልላዊና ዓለም አቀፋዊ ችግሮችን ከማባባስ ይልቅ መፍትሄዎችን ለማፈላለግ ያለመ መሆኑ ተነግሯል
ሁለት ደርዘን የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች በኢንዶኔዥያ ይመክራሉ።
የአሜሪካ-ቻይና ፉክክር፣ በዩክሬን ያለው ጦርነት እና የሰሜን ኮሪያ ሚሳይል በደቡብ ምስራቅ እስያ ዓመታዊ የጸጥታ ስብሰባ ላይ የክብ ጠረጴዛ ንግግሮችን ለመቆጣጠር ተዘጋጅተዋል።
የቻይና፣ የአሜሪካ እና የሩሲያ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች በክልላዊ ፎረሙን ለመቀላቀል ከተዘጋጁት መካከል ይገኙበታል።
የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት ማህበር ሊቀመንበር እና የኢንዶኔዥያ ፕሬዝዳንት ጆኮ ዊዶዶ፤ ጉባኤው ክልላዊ እና ዓለም አቀፋዊ ችግሮችን ከማባባስ ይልቅ መፍትሄዎችን ለመፈለግ ያለመ ነው ብለዋል።
"እኛ እያደግን ያለን ሀገራት የዜሮ ድምር አካሄድን ትተን ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደርግ የመፍትሄ አቅጣጫ እንድንይዝ ማስተዋል፣ ጥበብ፤ ከጎረቤቶቻችን ደግሞ ድጋፍ እንፈልጋለን" ሲሉ አክለዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ትናንት ሀሙስ በጃካርታ ከቻይና ከፍተኛ ዲፕሎማት ዋንግ ዪ ጋር "ታማኝ እና ገንቢ" ውይይት ማካሄዳቸውን መስሪያ ቤታቸው ገልጿል።