ወደ ፖርት ሱዳንና ሱዋኪን ወደቦች የሚወስደው ዋና መንገድ በሬድሲ ግዛት አቃባን ጨምሮ በሶስት ቦታዎች ላይ ተዘግቷል
የቤጃ ጎሳ አባላት የሆኑ ተቃዋሚዎች በምስራቅ ሱዳን ያሉ ወደቦችን ከሌሎች የሀገሪቱ ክፍል ጋር የሚያገኘውን መንገድ ዘግተዋል፡፡ ለተቃውሞ መነሻ የሆነው የቤጃ ጎሳ አባላት የሚኖሩበት ግዛት ኋላ ቀር ነው የሚል መሆኑን የተለያዩ ሚዲያዎች እየዘገቡት ይገኛሉ፡፡
የቤጃ ጠቅላይ ም/ቤት ተብሎ የሚጠራው የቤጃ ጎሳ አባላት ተቆርቋሪ ያሰማውን ጥሪ ተከትሎ ዋናው መንገድ አምስት ቦታዎች በላይ መዘጋቱ ተዘግቧል፡፡
ወደ ፖርት ሱዳንና ሱዋኪን ወደቦች የሚወስደው መንገድ በሬድሲ ግዛት አቃባን ጨምሮ በሶስት ቦታዎች ላይ የተዘጋ ሲሆን ከግብጽ ጋር የሚያገናኘው ኦሲፍ መንገድም በተቃውሞ መዘጋቱ ተገልጿል፡፡
ከሬድ ሲግዛት በተጨማሪ በከሰላ ግዛት በሁለት ቦታዎችና በገዳሪፍ ግዛት በሶስት ቦታዎች መዘጋቱም ተዘግቧል፡፡
ሱዳን በዳርፉር ተፈጽሟል ከተባለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር ስሟ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡
በፈረንጅቹ 2003 ዓመት አንስቶ በዳርፉር በተከሰተ የጎሳ ግጭት 300 ሺህ ዜጎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ ከመኖሪያ ቀዬአቸው እንደተፈናቀሉ የመንግስታቱ ድርጅት ሪፖርት ያስረዳል።
ይሄንን አደጋ ለማስቆምም የተመድ-አፍሪካ የተቀናጀ ዘመቻ ሰላም የማስከበር ስራ ፕሮግራም ሲተገር የቆየ ሲሆን ከ16 ሺህ በላይ ሰላም አስከባሪ ጦር በስፍራው ተሰማርቶ ነበር።ይሁንና ይህ የሰላም ማስከበር ዘመቻ ካሳለፍነው ታህሳስ ወር ጀምሮ እንዲቆም ድርጅቱ ውሳኔ ቢያሳልፍም በዳርፉር አሁንም ዜጎች በሚሊሻዎች ሲገደሉ እና ሲፈናቀሉ ይታያል።
ሱዳንን ለ30 አመታት ሲያስተዳድሩት የነበሩትና ከ3 አመት በፊት በተነሳባቸው ህዝባዊ አመጽ ከስልጣን የተነሱት የቀድሞው ፕሬዘዳንት ኦማር አልበሽር የዘር ማጥፋት ወንጅል ፈጽመዋል ተብለው ተወንጅለዋል፡፡ አሁን በሱዳን በእስር ላይ የሚገኙት አልበሽር ጉዳያቸው በአለምአቀፉ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት እንዲታይ ተላልፈው ሊሰጡ መሆኑም ተሰምቷል፡፡