ቦይንግ ኩባንያ በምርቶቹ ላይ በደረሱበት ተደጋጋሚ የቴክኒክ ችግሮች ኪሳራዎችን በማስተናገድ ላይ ይገኛል
ቦይንግ ኩባንያ አዲስ ስራ አስፈጻሚ ሾመ።
የዓለማችን ግዙፉ የአቪዮሽን ተቋም ቦይንግ ዳይሬክተሮች ቦርድ አዲስ ፕሬዝዳንት መርጧል።
ድርጅቱ እንዳስታወቀው በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከ35 ዓመት በላይ ልምድ ያላቸው ሮበርት ኬሊ አዲሱ የቦይንግ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል።
ላለፉት አራት ዓመታት የቦይንግ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዴቭ ካልሁን ራሳቸውን ከሀላፊነት አንስተዋል።
የዓለማችን ቁጥር አንድ የአቪዬሽን ኩባንያ የሆነው ቦይንግ በተለይም ካሳለፍነው ጥር ወር ጀምሮ በምርቶቹ ላይ የጥራት ጉድለቶች አጋጥመዋል።
737 ማክስ 9 የተሰኘው አውሮፕላን በበረራ ላይ እያለ የመስኮት እና በር መገንጠል አጋጥመው ነበር።
ይህን ተከትሎ ቦይንግ ኩባንያ ያመረታቸው ምርቶች የጥራት ጉድለቶች እንዳሉ የቀድሞው የድርጅቱ ሰራተኞች ሳይቀር መረጃዎችን ለብዙሀን መገናኛዎች ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ቦይንግ ስሪት የሆኑ በርካታ አውሮፕላኖች በተለያዩ ሀገራት እክል አጋጥሟቸው ታይተዋል።
በነዚህ የምርት ጉድለቶች ምክንያትም ቦይንግ ኩባንያ በርካታ ትችቶችን ያስተናገደ ሲሆን በኩባንያው ገቢ ላይም ጉዳት አድርሷል።
ለአብነትም በምርት ጥራት ጉድለት ምክንያት ምርቶችን ለደንበኞች በወቅቱ አለማስረከብ፣ ከዚህ በፊት በነበረው ልክ የአዳዲስ አውሮፕላን ግዢዎች ትዕዛዝ መጠን መቀነስ እና የገቢ መቀነሶች ዋነኞቹ ናቸው።
ቦይንግ ኩባንያ ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ብቻ የ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደደረሰበት አስታውቋል።
አዲሱ ፕሬዝዳንት ሮበርት ኬሊ ቦይንግ የገጠመውን የምርት ትራት ጉድለት እና ሌሎች ችግሮችን መፍታት እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል።
የመካኒካል ምህንድስና ምሩቅ የሆኑት አዲሱ የቦይንግ ፕሬዝዳንት የአሜሪካ ኤሮስፔስ ማህበር ፕሬዝዳንት ሆነው አገልግለዋል።
በ150 ሀገራት ምርቶቹን የሚሸጠው ቦይንግ በመላው ዓለም 170 ሺህ ሰራተኞችም አሉት።