ሩሲያ በፓሲፊክ ቀጣና አሜሪካን ለመመከት ከቻይና ጋር በመሆን ወታደራዊ ልምምድ እያደረገች ነው
ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን አሜሪካ በእስያ ሞስኮን ለመብለጥ ሙከራ እያደረገች ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል
ፑቲን ሩሲያ ለየትኛውም ሁኔታ ዝግጁ መሆን እንዳለባት እና የባህር ኃይሏን ማጠናከሯን እንደምትቀጥል ተናግረዋል
ሩሲያ በፓሲፊክ ቀጣና አሜሪካን ለመመከት ከቻይና ጋር በመሆን ወታደራዊ ልምምድ እያደረገች ነው።
ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ ከከሶቬት ህብረት መፈራረስ ወዲህ ከቻይና ጋር በመሆን ትልቁን የሩሲያ የባህር ኃይል ልምምድ ማድረግ በጀመረችበት በትናንትናው እለት አሜሪካ በእስያ ሞስኮን ለመብለጥ ሙከራ እያደረገች ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ፑቲን እንደገለጹት 'ኦሽን-2024' የተባለው ስትራቴጂካዊ ልምምድ ከሜዲትራኒያን ባህር እስከ ፖስፊክ ያለውን ቦታ የሚሸፍን ሲሆን የባህር ኃይል ዩኒቶችን የመዋጋት አቅም እና የጦር መሳሪያ አጠቃቃም ይፈትሻል።
ልምምዱ ሩሲያ በዩክሬን እያደረገች ካለው "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" የተገኙ ልምዶችንም እንደሚያካትት ተገልጿል። "ከወዳጅ ሀገራት ጋር ወታደራዊ ትብብር ለማጠናከር ልዩ ትኩረት ሰጥተናል" ሲሉ ፑቲን ልምምዱ በተጀመረበት ወቅት ለባለስልጣናት ተናግረዋል።
"በአሁኑ ወቅት እያደገ ከመጣው የጂኦፖለቲካ ውጥረት አንጻር ሲታይ ይህ በጣም አስፈላጊ ነው። አሜሪካ የትኛውንም ዋጋ ከፍላ ያላትን አለማቀፋዊ የወታደራዊ እና የፖለቲካዊ የበላይነት ለማስጠበቅ እየሞከረች ነው" ብለዋል ፑቲን።
ፑቲን በዋሽንግተን ቀስቃሽነት አለምአቀፍ የጦር መሳሪያ ማምረት ፉክክር ስለተፈጠረ ሩሲያ ለየትኛውም ሁኔታ ዝግጁ መሆን እንዳለባት እና የባህር ኃይሏን ማጠናከሯን እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
"ከሩሲያ የሚቃጣ ስጋት አለ በሚል ሰበብ እና ቻይናን ባለችበት ለማስቆም፣ አሜሪካ እና አጋሮቿ በሩሲያ ምዕራባዊ ድንበር አቅራቢያ፣ በአርክቲክ እና በእስያ ፓሲፊክ ቀጣና ወታደራዊ ስምሪታቸውን ጨምረዋል" ብለዋል ፑቲን።
"አሜሪካ እና አጋሮቿ የአጭር ርቀት እና የረጅም ርቀት ሚሳይሎቻቸውን ሩሲያን ለማጥቃት በሚያስችል ርቀት ላይ ለማጥመድ እቅድ እንዳላቸው በግልጽ ተናግረዋል።"
አሜሪካ በበኩሏ በፓሲፊክ ቀጣና ያላት አጋርነት ቀጣናውን ለማረጋጋት ወታደራዊ ትብብር ለማጠናከር ያለመ ነው ማለቷ ይታወሳል።
ፑቲን ግን ይህ የአሜሪካ እንቅስቃሴ በቀጣናው ያለውን የኃይል ሚዛን ለማዛባት ነው ይላሉ። የባህር ኃይል አዛዥ የሆኑት አሌክሳንደር ሞይሴየቭ በዚህ ልምምድ ላይ አራት የቻይና መርከቦች እና 15 አውሮፕላኖች እየተሳተፉ ይገኛሉ።