ሮማ ጆዜ ሞሪንሆን አሰናበተ
ለፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ስንበት ክለቡ በላዚዮ እና ኤሲ ሚላን የደረሰበት ሽንፈትና በሴሪአው 9ኛ ደረጃ መቀመጥ በምክንያትነት ተጠቅሰዋል
የ60 አመቱ አወዛጋቢ ሰው በቀጣይ የፖርቹጋል ብሄራዊ ቡድንን ለማሰልጠን ሊስማሙ ይችላሉ ተብሏል
ሮማ አሰልጣኙን ጆዜ ሞሪንሆን በይፋ ማሰናበቱን አስታወቀ።
የጣሊያኑ ክለብ ባለቤቶች ዳን እና ሪያን ፍሬድኪን ሞሪንሆን “ላሳዩት የስራ ፍቅርና ትጋት” አመስግነው ከስራቸው እንዳሰናበቷቸው ገልጸዋል።
“የጆዜ ድንቅ የአመራር ክህሎት ሁሌም የምናስታውሰው ነው፤ ነገር ግን ለክለቡ ጥቅም መከበር ሲባል ለውጥ መደረጉ (ስንብታቸው) የግድ ነው” ብለዋል ባለቤቶቹ ባወጡት መግለጫ።
ለፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ስንብት ባለፈው ሳምንት በላዚዮ ተሸንፈው ከኮፓ ኢታሊያ መሰናበታቸው አንደኛው ምክንያት ነው ተብሏል።
ባለፈው እሁድ በከተማ ተቀናቃኛቸው ኤሲ ሚላን 3 ለ 1 ተሸንፈው በሴሪአው 9ኛ ደረጃ (ከመሪው ኢንተርሚላን በ22 ነጥብ ዝቅ ብለው) መቀመጣቸውም የክለቡን ባለቤቶች ከዚህ ውሳኔ ላይ እንዳደረሳቸው ተገልጿል።
በግንቦት ወር 2021 የጣሊያኑን ክለብ ማሰልጠን የጀመሩት አወዛጋቢው አሰልጣኝ በ2022 ሮማን የኮንፈረንስ ሊግ ዋንጫ ባለቤት ማድረግ መቻላቸው ይታወሳል።
ይህም በሮማ ደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ አስችሯቸው እንደነበር አይዘነጋም።
ይሁን እንጂ ባለፈው አመት የዩሮፓ ሊግ ፍጻሜ ላይ ሲቪያ በፍጹም ቅጣት ምት ካሸነፋቸው በኋላ ድል ርቋቸዋል።
በስድስት የሴሪአ ጨዋታዎች ያስመዘገቡት አምስት ነጥብም የክለቡ ደካማ አጀማመር ነው ተብሎ የ60 አመቱ አሰልጣኝ ላይ ጫና እንዲበረታ ማድረጉ ይታወሳል።
ራሳቸውን “ልዩው ሰው” እያሉ የሚጠሩት ሞሪንሆ ግን ሮማ “የካበተ ልምዴን በማየት ብዙ ይጠብቃል” በሚል ወቀሳውን ከትከሻቸው ለማውረድ ሲሞክሩ ታይተዋል።
የቀድሞው የቼልሲ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ቶትንሃም አሰልጣኝ ከሮማ ጋር የነበራቸው ኮንትራት በዚህ የውድድር አመት መጨረሻ ይጠናቀቅ ነበር።
ካሰለጠኗቸው ክለቦች የመባረር አጋጣሚ የተደጋገመባቸው ሞሪንሆ በቀጣይ የፖርቹጋል ብሄራዊ ቡድንን በአሰልጣኝነት ሊይዙ እንደሚችሉ ይገመታል።
ሙሉ ትኩረቴን ሮማ ላይ ማድረግን መርጫለሁ በሚል የብሄራዊ ቡድኑን አሰልጣኝነት እንደማይቀበሉ ሲገልጹ የቆዩት ጆዜ ቀጣይ እቅዳቸውን አላሳወቁም።