የ5 ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊው ከቤተሰቦቹ ጋር ነው ለማክሰኞ አጥቢያ ሪያድ የገባው
ፖርቹጋላዊው ተጫዋች ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከሳኡዲ አረቢያው ክለብ አል ናስር ጋር ውሉን ለመጨረስ ሪያድ ገብቷል።
የ37 አመቱ ኮከብ ከቤተሰቦቹ ጋር ሌሊቱን ሪያድ ሲገባ የክለቡ ፕሬዝዳንት ሙሳሊ አል ሙአመር፣ ምክትል ፕሬዝዳንቱ አብዱላህ ቢን አብዱራሂም አል ኦምራኒን ጨምሮ የክለቡ ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል አድርገውለታል።
የ5 ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊው በዛሬው እለት የጤና ምርመራ የሚያደርግ ሲሆን፥ ውሉን ካጠናቀቀ በኋላም በናስር ኤም አር ሶል ፓርክ ከደጋፊዎች ጋር ይተዋወቃል።
የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ አጥቂ ባለፈው አርብ ለአል ናስር ክለብ ለሁለት አመት ተኩል ለመጫወት መስማማቱን መግለጹ የሚታወስ ነው።
በአል ናስር በአመት 200 ሚሊየን ዶላር የሚከፈለው ሮናልዶ የአለማችን ውዱ ተጫዋች ሆኗል።
የሳኡዲን ሊግ እየመራ ያለው አል ናስር ስምንት ጊዜ ሻምፒዮን በሆነበት ሊግ የሮናልዶ መካተት ትልቅ ገበያ ይዞ እንደሚመጣ ይጠበቃል።
ሮናልዶም “በአዲስ ሊግ በአዲስ ሀገር የተለይ ልምድ በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ” ብሏል።
አል ናስር በወንዶችም ሆነ በሴቶች እግር ኳስ ላይ እየሰራ ያለውን ስራ ያደነቀው ተጫዋቹ፥ ሳኡዲ አረቢያ በአለም ዋንጫው ያሳየችው ብቃት የእግር ኳስ አቅሟን ያሳየ መሆኑን ገልጿል።
በአውሮፓ ያገኘውን ስኬትና ልምድ በእስያ ማጋራት እንደሚፈልግ በማንሳትም ከክለብ አጋሮቹ ጋር ልምምድ ለመስራት መጓጓቱን መናገሩን ዘናሽናል ኒውስ አስነብቧል።
አምስት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ያነሳው ፖርቹጋላዊ በእንግሊዝ፣ በስፔን እና ጣሊያን ሰባት የሊግ ዋንጫዎችን ማንሳት ችሏል።
በ2016 ፖርቹጋልን ለአውሮፓ ዋንጫ ያበቃው ክርስቲያኖ ሮናልዶ፥ አምስተኛውን የአለም ዋንጫ ተሳትፎ በኳታር አድርጎ ጎል በማስቆጠርም ታሪክ ሰርቷል።
ከፒርስ ሞርጋን ጋር ባደረገው ቃለምልልስ የማንቸስተር ዩናይትድን አሰልጣኝ እና የክለብ አጋሮቿን ያብጠለጠለው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከክለቡ ጋር በስምምነት ከተለያየ በኋላ ክለብ አልባ ሆኖ ቆይቷል።
የሳኡዲው አል ናስር ክለብም የአለማችን ኮከብ መዳረሻ ሆኗል።