ሮናልዶ ወደ ሳኡዲ እንዲመጡ የጋበዛቸው አራት የዩናይትድ ተጨዋቾች እነማን ናቸው?
ተጨዋቾቹ የሚመቻቸው ከሆነ በበዓል ቀን አብረውት እንዲሆኑ የሮናልዶ ፍላጎት ነው ተብሏል
ሮናልዶ ግብዣ ካቀረበላቸው ተጨዋቾች መካከል እንግሊዛዊው ሃሪ ማጉዌር ይገኝበታል
ከፒርስ ሞርጋን ጋር ያደረገውን አወዛጋቢ ቃለ ምልልስ ተከትሎ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ኦልድትራፎርድን ለቆ የወጣው ፖርቹጋላዊው ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ የማንቸስተር ዩናይትድ የቡድን አጋሮቹን የመሰናበት እድል እንኳን እንደተነፈገው የሚታወስ ነው፡፡
በዚህ ደስተኛ ያልሆነው ሮናልዶ አሁን ላይ ከእሱ ጋር ጥሩ የሚባል ግንኙነት የነበራቸው አራት የክለቡ ተጨዋቾች ወደ ሳኡዲ አረቢያ መጥተው የአል-ናስርን ጨዋታ እንዲመለከቱና አብረውት ጥሩ የጓደኝነት ጊዜያት እንዲያሳልፉ ግብዣ ማቅረቡ እየተነገረ ነው፡፡
- የሳኡዲው ክለብ አል ናስር ለሽንፈቱ ፖርቹጋለዊውን ኮከብ ሮናልዶን ተጠያቂ አደረገ
ሮናልዶ ግብዣ ያቀረበላቸው የማንቸስተር ዩናይትድ ተጨዋቾች ሃሪ ማጓየር፣ ብሩኖ ፈርናንዴዝ፣ ካሴሚሮ እና ራፋኤል ቫራን ናቸው፡፡
እንደ ዘ-ሰን ጋዜጣ ዘገባ ከሆነ ተጨዋቾቹ የሚመቻቸው ከሆነ በበዓል ቀን አብረውት እንዲሆኑ የሮናልዶ ፍላጎት ነው፡፡
ተጨዋቾቹ ወደ ሳኡዲ አረቢያ መምጣት የማይመቻቸው ከሆነ ደግሞ በፖርቹጋል ሊዝበን እየተገነባ ባለው መኖሪያ ቤቱ ሊገኛኙ እንደሚችሉ ሮናልዶ አማራጭ ሀሳብ አቅርቧል፡፡
የአምስት ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊው ሮናልዶ የማንቸስተርን ቤት ለቆ ከወጣ በኋላ የቅንጦት መኪናዎቹን ወደ ፖርቹጋል በማዛወር ኑሮውን በሊዝበን ማድረጉ አይዘነጋም፡፡
በማንቸስተር ቤት ብዙ ምቾት ያልነበረው ሮናልዶ ከኳታሩ የዓለም ዋንጫ በኋላ በ170 ሚሊዮን ፓውንድ የሳኡዲውን ክለብ አል-ናስር መቀላቀሉ የሚታወስ ነው፡፡
ሮናልዶ በሳኡዲ ፕሮፌሽናል ሊግ የራሱን አሻራ ያኖራል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ ይሁን እንጂ ፖርቹጋላዊው ኮከብ ከአሁኑ ትችቶች ማስተናገድ ጀምሯል።
አዲሱ የሮናልዶ ክለብ አል-ናስር ባሳለፈው ሐሙስ ምሽት በነበረው የሱፐር ካፕ የግማሽ ፍታሜ ጨዋታ በአል-ኢትሃድ 3 ለ 1 በሆነ ውጤት ተሸንፎ ከውድድሩ ውጭ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ክለቡ ታዲያ ለደረሰበት ሽንፈት ክርስቲያኖ ሮናልዶን ተጠያቂ አድርጓል፡፡
የአል-ናስር ስራ አስኪያጅ ሩዲ ጋርሺያ ሮናልዶ በመጀመሪያው አጋማሽ የተፈጠሩትን የጎል እድሎች አለመጠቀሙ ቡድኑን ዋጋ አስከፍሎታል ማለታቸው አይዘነጋም፡፡
የሮናልዶ እድሎችን አለመጠቀም “የጨዋታውን ሂደት ቀይሯል” ሲሉም ነበር የተናገሩት ሩዲ ጋርሺያ።