በሱዳን ጦርነት እስካሁን 20 ሺህ ሰዎች ተገድለዋል- ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም
በሱዳን ጉብኝት ያደረጉት ዶ/ር ቴድሮስ የሟቾች ቁጥር ከዚህም ሊያሻቅብ ይችላል ብለዋል
ከተጀመረ 16 ወራትን ያስቆጠረው የሱዳን ጦርት በርካታ ቀውሶችን አስከትሏል
በሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ቢያንስ 20 ሰዎች መገደላቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም አስታወቁ።
በሱዳን ያደረጉትን የሁለት ቀናት ጉብኝት ማጠናቀቃቸውን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት ዶ/ር ቴድሮስ፤ የሟቾች ቁጥር ከዚህም ሊያሻቅብ እንደሚችል አስታውቀዋል።
ዶ/ር ቴድሮስ መግለጫውን የሰጡት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ እውቅና የተሰጠው የሱዳን ጦር መቀመጫ በመሆን እያገለገለች ባለችው ፖርት ሱዳን ከተማ ነው።
“ሱዳን ከፍተኛ በሆነ የችግር ማዕበል እየተሰቃየች ነው” ያሉት ዶ/ር ቴድሮስ፤ “ጦርነቱ ያስከተለው አደጋ መጠን አስደንጋጭ ነው፣ ሆኖም ግን ግጭቱን ለመግታት በቂ እርምጃ እየተወሰደ አይደለም” ብለዋል።
“ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲነቃ እና ሱዳንን ካለችበት ቅዠት እንዲያስወጣት ጥሪ እናቀርባለን” ያሉት ዶ/ር ቴድሮስ፤ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል።
“በጣም ምርጡ መድሃኒት ሰላም ነው” ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የሱዳን ጦርነት ባሳለፍነው 2015 መጋቢት ወር ላይ የተቀሰቀሰ ሲሆን፤ የሱዳን ጦር እና የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መመካከል የነበረው ፍጥጫ ወደ ግጭት ማምራቱን ተከትሎ ነው ጦርነቱ የተቀሰቀሰው።
ግጭቱ ዋና ከተማዋን ካርቱምን ጨምሮ ሌሎች ከተሞችን ወደ ጦር ሜዳነት የቀየረ ሲሆን የጤናን ጨምሮ የሲቪል መሰረተ ልማቶችም በጦርነቱ ወድመዋል።
ጦርነቱ የዓለምችንን ግዙፉን የሰዎች መፈናቀል ያስከተለ ሲሆን፤ በጦርቱ እስካን ከ13 ሚሊየን በላይ ሱደናውያን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ ከእነዚህም ውስጥ 2.3 ሚሊየን ሱዳናውያን ወደ ጎረቤት ሀገራት መሰደዳቸውን ነው ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ያስታወቀው።
የተባሩት መንግስታ ድርጅት (ተመድ) ከሰሞኑ በሱዳን የሰላም አስከባሪ ሀይል እንዲሰማራ መጠየቁ ይታወሳል።
ወሲባዊ ባርነትን ጨምሮ ሌሎች የመብት ጥሰቶች በሁለቱም አካላት እየተፈጸሙ ነው ያለው ተመድ በንጹሀን ላይ የሚደርሱ በደሎችን ለመቀነስ ገለልተኛ የሰላም አስከባሪ ሀይል እንዲገባ ጠይቋል።
ጦርነቱ በአሁኑ ወቅት ሱዳን ካሏት 18 ክልሎች መካከል በ14ቱ ክልሎች የተስፋፋ ሲሆን፤ የዜጎች ደህንነት ለአደጋ የመጋለጥ እድሉ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ እንደሚገኝ ተመላክቷል።