ተመድ እስራኤል በፍልስጤም የምታደርገውን የመሬት ወረራ እንድታቆም አለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲያደርግ ጠየቀ
ከጦርነቱ መጀመር በኋላ እስራኤል በፍልስጤም እያረገችው ያለው መስፋፋት ጨምሯል ተብሏል
እስራኤል ለዚህ ወቀሳ በሰጠችው ምላሽ ወደ አንድ ወገን ያዘነበለ ፍትሀዊ ያልሆነ ሀሳብ ስትል አጣጥላለች
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር እስራኤል የፍልስጤምን መሬት ለመቆጣጠር እያደረገች ያለችውን ህገወጥ ተግባር አለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያስቆም ጠይቀዋል፡፡
ቅድሚያ የሚሰጠው ጦርነቱን ማስቆም ቢሆንም ጎን ለጎን ቴልአቪቭ ከጋዛው ጦርነት መጀመር በኋላ በፍልስጤም እያደረገች ያለችው መስፋፋት በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ ነው ብለዋል፡፡
በጄኔቫ እየተካሄደ በሚገኝው የተመድ ሰብአዊ መብቶች ካውንስል ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ቮልከር ተርክ ሀገራት የተመድም ሆኖ ሌሎች አለም አቀፋዊ ህጎች በማን አለብኝነት ሲጣሱ ዝም ሊሉ አይገባም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እስራኤል በዌስት ባንክ እና በአካባቢው በአዲስ መልክ የፍልስጤም ግዛቶችን ለመቆጣጠር እያደረገች በምትገኘው ጥረት ሰብአዊ መብቶች እየተጣሱ ንጹሀንም እየተገደሉ ነው ተብሏል፡፡
በነዚህ ጥቃቶች ላይ ከመከላከያ ሀይሉ ባለፈ ዜጎችም እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተመድ ተደጋጋሚ ጥቆማዎች እየደረሱት እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
እስራኤል ለዚህ ወቀሳ በሰጠችው ምላሽ ነባራዊ ሁኔታዎችን ያላጤነ ለአንድ ወገን ብቻ ውግንና ያለው ሀሳብ ስትል አጣጥላዋለች፡፡
በሲውዘርላንድ ጄኔቫ እየተካሄደ በሚገኘው አመታዊ ጉባኤ ላይ በፖለቲካዊ አስተዳደር መዳከም የተነሳ በአለም አቀፍ ደረጃ እየተበራከቱ ስለሚገኙ ግጭቶች እና ብጥብጦች ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ዩክሬን ፣ አፍጋኒስታን እና በሱዳን እየተካሄደ የሚገኝው ጦርነት በውይይቱ ከሚዳሰሱ አካባቢዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
በአፍጋኒስታን እየጨመረ የመጣው የሞት ቅጣት እንዲሁም በስነ ምግባር ህጎች ስም የዜጎች ሰብአዊ መብት እየተጣሰ እንደሚገኝ የተባበሩት መንገስታት ድርጅት የሰበአዊ ኮሚሽን ኮሚሽነር ቮለከር ተርክ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በብሪታንያ ፣ አሜሪካ እና ጀርመንን በመሳሰሉ ምእራባውያን ሀገራት ምርጫ በደረሰ ቁጥር ከስደተኞች ጋር ተያይዘው የሚነሱ አጀንዳዎች ለብጥብጥ እና ለሰብአዊ መብት ጥሰት እየሆኑ እንደሚገኙ አክለዋል፡፡