የረሃብ አድማ ላይ የነበሩት የስፔን እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት እናት ከሆስፒታል ወጡ
“ልጄ ላይ የሚሰነዘር ትችት እስካልቆመ ድረስ የረሃብ አድማዬን እቀጥላለሁ” ያሉት እናት ታመው ትናንት ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል
የ72 አመቷ አዛውንት ልጃቸውን በፊፋ ከመታገድ ባይታደጉትም እናት ለልጇ ማድረግ የምትችለውን ለአለም አሳይተዋል
የዘንድሮውን የሴቶች የአለም ዋንጫ የስፔን ድል ያደበዘዘው የ”ከንፈር ቅሌት” አሁንም መነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ቀጥሏል።
ጀኒ ሄርሞሶ የተባለችውን ተጫዋች ከንፈር የሳሙት የስፔን እግርኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት ልዊስ ሩቤልስ እናት ታመው ሆስፒታል መገባታቸው ትናንት የመገናኛ ብዙሃን ትኩረት ነበር።
አንጅለስ ቤጃር የተሰኙት የሩቤልስ እናት ልጃቸው በስፔን ብሎም በአለማቀፍ ደረጃ የደረሰበት ውግዘት “አይገባውም” ብለው የረሃብ አድማ መጀመራቸው ይታወሳል።
ሩቤልስ ባደጉበት ከተማ በሚገኘው “ዲቪና ፓስቶራ” ቤተክርስቲያን ውስጥም በር ዘግተው ሌትም ቀንም ለልጃቸው መጸለይ ጀምረው ነበር።
“በልጄ ላይ የሚደርሰው ውግዘት እስካልቆመ ድረስ የረሃብ አድማዬን እቀጥላለሁ” ማለታቸውም አይዘነጋም።
ትናንት ለጋዜጠኞች መግለጫ ይሰጣሉ ተብለው ሲጠበቁ ግን አንቶኒዮ የተባሉ የሃይማኖት አባት “አንጅለስ ቤጃር በዚህ የሉም፤ ታመው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል” የሚል መረጃን ለሬውተርስ ተናግረዋል።
ከሶስት ቀናት የረሃብ አድማ በኋላ እናት አንጅለስ ክፉኛ መዳከማቸውን ተከትሎ ሞትሪል በተሰኘችው ከተማ ወደሚገኘው ሳንታና ሆስፒታል መወሰዳቸውንም በማከል።
የ72 አመቷ አዛውንት ለስድስት ስአታት ህክምና የተደረገላቸው ሲሆን፥ ከ10 ቀናት በላይ የመላው አለም መነጋገሪያ የነበረው ልጃቸው ልዊስ ሩቤልስ ሆስፒታል ድረስ መጥቶ ወደ ቤት ወስዷቸዋል ተብሏል።
ልጃቸውን ከስድብና ውግዘት በጸሎት ሃይል ለማትረፍ የረሃብ አድማ ጀምረው የነበሩት እናት ከሞት አፋፍ ተመልሰዋል፤ ሩቤልስን በፊፋ እና በስፔን ከመታገድ ባይታደጉትም ቢያንስ እናት ለልጇ ማድረግ የምትችለውን ለአለም አሳይተዋል።
እንግሊዝን በማሸነፍ የሴቶች የአለም ዋንጫን ያነሳው የስፔን ብሄራዊ ቡድን ድል የ”ከንፈር ቅሌት” የሚል ስያሜ በተሰጠው የሩቤልስ እና ሄርሞሶ መሳሳም መደብዘዙ በርካታ የስፖርት ቤተሰቦችን አስቆጭቷል።
የመብት ተከራካሪዎች ግን የስፔን እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንቱ ድርጊት በወሲባዊ ትንኮሳ የሚያስከስስ ጭምር አድርገው እያቀረቡት ሲሆን፥ ክስ ለመመስረትም ምርመራ የጀመሩ የህግ ባለሙያዎች አሉ ተብሏል።
ልዊስ ሩቤልስ ግን “ከተጫዋቿ መልካም ፈቃድ ቢኖር ነው የተሳሳምነው” በሚል የሚቀርብባቸውን ወቀሳ ሲያጣጥሉት ቆይተዋል።
የአለማቀፉ የእግር ኳስ ማህበርም ፕሬዝዳንቱ በገዛ ፈቃዳቸው ከሃላፊነት እንዲለቁ ቢጠይቃቸው እምቢታን ስለመረጡ ባለፈው ቅዳሜ እንዳገዳቸው የሚታወስ ነው።