ሩሲያ ከቻይና ጋር በመሆን በጨረቃ ላይ የኑክሌር ኃይል ጣቢያ ለማቋቋም ማቀዷን ገለጸች
ቻይና ባለፈው ወር እስከ ፈረንጆቹ 2030 ባለው ጊዜ ውስጥ የመጀመሪያውን የቻይና ጠፈርተኛ ጨረቃ ላይ ለማሳረፍ ማቀዷን አስታውቃለች
የቀድሞ ምክትል መከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ቦሪሶቭ ሩሲያ እና ቻይና በሉናር ፕሮግራም ላይ በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ነው ብለዋል
ሩሲያ ከቻይና ጋር በመሆን በጨረቃ ላይ የኑክሌር ኃይል ጣቢያ ለማቋቋም ማቀዷን ገለጸች።
ሩሲያ እና ቻይና በቅንጅት በመሆን በፈረንጆቹ ከ2033-35 በጨረቃ ላይ የኑክሌር ኃይል ጣቢያ ለማቋቋም እያሰቡ መሆናቸውን የሩሲያ ስፔስ ኤጀንሲ ሮዝኮስሞስ ኃላፊ ዩሪ ቦርሶቭ በትናንትናው እለት ተናግረዋል።
የቀድሞ ምክትል መከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ቦሪሶቭ ሩሲያ እና ቻይና በሉናር ፕሮግራም ላይ በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ነው ብለዋል።
ቦሪሶቭ እንደገለጹት በዚህ የጋራ ፕሮግራም ላይ የሩሲያ "የስፔስ ኑክሌር ኢነርጂ" ባለሙያዎች አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።
"በአሁኑ ወቅት ከ2033-35 ባለው ጊዜ ውስጥ ከቻይና አጋሮቻችን ጋር በመሆን በሉናር ሰርፊስ(በጨረቃ) ላይ የኑክሌር ጣቢያ ለማቋቋም በትኩረተ እየሰራን ነው" ብለዋል ቦሪሶቭ።
ኃላፊው ወደፊት በጨረቃ ላይ ለሚደረገው ሰፈራ የሶላር ኃይል በቂ እንዳልሆነ እና የኑክሌር ኃይል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ቦሪሶቭ "ይህ ከባድ ፈተና ነው...ያለሰው እና በአውቶማቲክ ሞድ መሰራት ያለበት ነው" ስሉ ስለእቅዱ ተናግረዋል።
ቦሪሶቭ ሩሲያ የጠፈር መንኮራኩሮችንም በኑክሌር ኃይል የማምጠቅ እቅድ እንዳላት ተናግረዋል።
የኑክሌር ማብላያው እንዴት ይቀዝቅዝ ከሚለው ውጭ ቴክኒክዊ የሆኑ የፕሮጀክቱ ጉዳዮች መፍትሄ አግኝተዋል ብለዋል ቦሪሶቭ።
የሩሲያ ባለስልጣን አንድ ቀን በጨረቃ ላይ ቁፋሮ እናደርጋለን ብለው አልመው የነበረ ቢሆንም የሩሲያ ስፔስ ፕሮግራም የተባለውን ያህል አልሄደም።
ሩሲያ ባለፈው አመት ከ47 አመታት በኋላ ያደረገችው የጨረቃ ተልዕኮ የጠፈር መንኮራኩሩ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ በመጋጨቱ ሳይሳ መቅረቱ ይታወሳል።
ቻይና ባለፈው ወር እስከ ፈረንጆቹ 2030 ባለው ጊዜ ውስጥ የመጀመሪያውን የቻይና ጠፈርተኛ ጨረቃ ላይ ለማሳረፍ ማቀዷን አስታውቃለች።
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን፣ ባለፈው ወር ሩሲያ በጨረቃ ላይ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ለማስቀመጥ አቅዳለች የሚለውን የአሜሪካ ማስጠንቀቂያ ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል።