ሩሲያ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ብትጠቀም ምን ሊከሰት ይችላል?
ዩክሬን በሞስኮ የቀረበባትን ክስ ውድቅ ብታደርግም ሩሲያ ግን ስለ "ደርቲ ቦምብ" ማውራቷን ቀጥላለች
ሩሲያ፤ ዩክሬን "ደርቲ ቦምብ" ለመጠቀም እየተዘጋጀች ነው የሚል ክስ አቅርባለች
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ጦርነት ከጀመረች ስምንት ወራት ሆኖታል፡፡
ይህ ጦርነት በየጊዜው አዳዲስ ክስተቶችን በማስተናገድ ላይ ሲሆን ከሰሞኑ ደግሞ የኑክሌር ጦር ጉዳይ መነሳት ጀምሯል፡፡
በሚያደርሰው ጉዳት ከኑክሌር ጦር መሳሪያ በመቀጠል የሚታወቀውን "ደርቲ ቦምብ" ዩክሬን ልትጠቀም ማቀዷን ሩሲያ ለጸጥታው ምክር ቤት እና ለወዳጅ ሀገራት በማሳወቅ ላይ ናት፡፡
ዩክሬን በሞስኮ የቀረበባትን ክስ ውድቅ ብታደርግም ሩሲያ ግን ስለ "ደርቲ ቦምብ" ማውራቷን ቀጥላለች።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጊ ሼጉ ከህንድ፣ ቻይና፣ አሜሪካ እና ሌሎችም ሀገራት መከላከያ ሚኒስትሮች ጋር ዩክሬን ልትጠቀመው ስላሰበችው "ደርቲ ቦምብ" በስልክ ተወያይተዋል፡፡
የሩሲያን አዲስ ዲፕሎማሲ ተከትሎ ሞስኮ ለምን ስለ "ደርቲ ቦምብ" ልትጨነቅ ቻለች የሚለው የብዙ ሀገራትን ትኩረት ስቧል፡፡
ዩክሬን ኑክሌር መለስ ቦምብ ወይም ደርቲ ቦምብን ጥቅም ላይ ለማዋል ዝግጁ መሆኗን ሩሲያ እርግጠኛ ሆና ሊሆን እንደሚችል ሲገለጽ በሌላ በኩል ደግሞ ሩሲያ ስለዚህ ቦምብ ማውራት የፈለገችው የኑክሌር አረሯን በዩክሬን ላይ ለመተኮስ ምክንያት እየፈለገች ሊሆንም ይችላል የሚሉ ሀሳቦችም በመነሳት ላይ ናቸው፡፡
ይሄንን ተከትሎም አሜሪካንን ጨምሮ ሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት ሩሲያ የኑክሌር ጦር መሳሪያ በዩክሬን ላይ ለመጠቀም ማሰቧን እየተናገሩ ናቸው፡፡
ሩሲያ የደርቲ ቦምብ ጥቃት ከዩክሬን ደረሰብኝ በሚል የኑክሌር ጦር መሳሪያዎቿን ብትጠቀም የዓለም ሀገራት ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል?
በለንደን የሚታተመው ታየም መጽሄት ሩሲያ የኑክሌር ጦር መሳሪያዋን በዩክሬን ላይ ብትጠቀም 10 ክስተቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ ሲል ተንታኞችን አነጋግሮ ዘለግ ያለ ጽሁፍ አስነብቧል፡፡
ኒጌል ዳቪስ የተሰኙት የሩሲያ ጉዳዮች ተንታኝ እንዳሉት ከተሞችን እና ነዋሪዎችን የሚጎዳው እና ራዲዮ አክቲቭ ያለው ደርቲ ቦምብ በዩክሬን ወደ ሩሲያ ከተተኮሰ ሞስኮ ተጨማሪ እና አዲስ ጥቃት በዩክሬን ላይ እንድትከፍት ሊያደርግ ይችላል ብለዋል፡፡
ሩሲያ በዚህ ቦምብ ከተጎዳች በዩክሬን የጀመረችውን ጦርነት ልታቋርጥ አልያም የኑክሌር ጦር መሳሪያዋን በዩክሬን ላይ ልትጠቀም ትችላለችም ተብሏል፡፡
ሩሲያ የኑክሌር ጦር መሳሪያዋን ከተጠቀመች አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት ብዙ ምላሽ ሊሰጡ እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡
ሩሲያ ከጸጥታው ምክር ቤት ማባረር የምዕራባዊያን የመጀመሪያው ድርጊት ሊሆን እንደሚችል የጠቆሙት እኝህ ተንታኝ ቻይና፣ ህንድ እና ሌሎች ሀገራት ሩሲያን በይፋ እንዲያወግዙ ከማድረግ ባለፈ ግንኙነታቸውን እንዲያቋርጡ ጫና ሊፈጥሩም ይችላሉም ተብሏል፡፡
የሩሲያ ሀብቶችን በመያዝ ለዩክሬን መልሶ ግንባታ እንዲውል ማድረግ ሌላኛው በሞስኮ ላይ ሊወሰድ የሚችል ድርጊት እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡
እንዲሁም ምዕራባዊያን ሀገራት ያላቸውን የጦር መሳሪያ ለዩክሬን በስፋት በመስጠት ሩሲያ እጅ እንድትሰጥ የማድረግ ውሳኔዎች ሊወሰኑ ይችላሉም ተብሏል፡፡
በተጨማሪም የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር የበረራ እገዳ ዞን በመከለል እና በሩሲያ ተቋማት ላይ የተቀናጀ የሳይበር ጥቃት በመሰንዘር ለዩክሬን ጦር የቀጥታ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚችልም ተጠቅሷል፡፡
እንደ ተንታኙ ግምት ከሆነ የመጨረሻው አማራጭ የሚሆነ በጥቁር ባህር ባለው የሩሲያ ወታደራዊ ማዘዣ ላይ ጥቃት መሰንዘር እና ሩሲያ የምድር፣ አየርም ሆነ የባህር ላይ ጥቃቶችን እንዳትሰነዝር ማድረግ ሊፈጸም እንደሚችል ተገልጿል፡፡
ይሁንና የኔቶ በቀጥታ ወደ ሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት መግባት እና ኑክሌር የጦር መሳሪያን መጠቀም በቀጥታ ሶስተኛውን የዓለም ጦርነት መጋበዝ እንደሚሆን ተንታኙ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል፡፡