አሜሪካ፤ ኢራን ተቃዋሚዎችን እንድታፍን ምክር የምትሰጣት ሩሲያ ናት ብላ እንደምታምን ገለጸች
የቴህራን ባለስልጣናት “ኢራን በተቃውሞ ሰልፎች እንድትናጥ ያደረገችው አሜሪካ ናት” ሲሉ ይከሳሉ
ዋሽንግተን፤ ተቃውሞን “አፍነዋል” በሚል በሰባት የኢራን ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ መጣሏ አይዘነጋም
ተቃውሞ “አፍነዋል” በሚል በሰባት የኢራን ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ የጣለችው አሜሪካ፤ ኢራን ተቃዋሚዎችን እንድታፍን ምክር የምትሰጣት ሩሲያ ናት ብላ እንደምታምን ገለጸች።
የዋይት ሃውስ የፕሬስ ሴክሬታሪ ካሪን ዣን ፒየር ዋሽንግተን "ሞስኮ ተቃዋሚዎችን በመጨፍለቅ ረገድ ያላትን ሰፊ ልምድ በመጠቀም ለኢራን ምክር ትሰጣለች ብላ ታምናለች” እናም ይህ ጉዳይ ያሳስበናል ብለዋል።
የዋይት ሀውስ የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ በበኩላቸው ክሬምሊን እንደዚህ አይነት እርምጃ አስቀድሞ ማዘዙን በተመለከተ ብዙም ግልጽ እንዳልነበረ መናገራቸው ኤ.ኤፍ.ፒ ዘግቧል።
“ተቃዋሚዎችን ለመጨፍለቅ በሚደረግ ጥረት የሚታዩ ጸጥታ ኃይሎች ድርጊቶች እያጤንን ነው” ያሉት ጆን ኪርቢ "በሚያሳዝን ሁኔታ ሩሲያ መሰል ልምድ እንዳለት" ተረድተናል ብለዋል።
አሜሪካ በኢራን የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ በተቃዋሚዎች ላይ ለሚወሰዱ እርምጃዎች ሞስንኮ ብትከስም የቴህራን ባለስልጣናት ግን ከጅምሩም ቢሆን ሀገሪቱ በተቃውሞ ሰልፎች እንድትናጥ ያደረገችው አሜሪካ ናት የሚል ክስ ሲያቀርቡ ተደምጠዋል።
የኢራን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ አሜሪካ በሀገሪቱ የተነሳውን ተቃውሞ ሽፋን በማድረግ ቴህራንን “የማተራመስ ፖሊሲ” እየተገበረች ነው ሲሉ በቅርቡ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
ራይሲ"የኢራን በውስጥ ጥንካሬዋ ላይ የተመሰረተ እድገት ማስመዝገብ ኃያላኖቹ ድንጋጤ ፈጥሮባቿል " ሲሉ ተናግረዋል።
የኢራን መሪ አያቶላ አሊ ካሜኒ በበኩላቸው የእስላማዊ ሪፐብሊክ ቀንደኛ ጠላቶች አሜሪካና እና እስራኤል “ሁከትና ብጥብጥ” እንዲቀሰቀስ አድርገዋል ሲሉ ከሰዋል።
"ዛሬ፤ ሁሉም ሰው በእነዚህ የጎዳና ላይ ረብሻዎች ውስጥ የጠላቶችን ተሳትፎ መኖሩ ያረጋግጣል"ም ነበር ያሉት አያቶላ አሊ ካሜኒ።
"እንደ ፕሮፓጋንዳ፣ በአእምሮ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር መሞከር፣ ደስታን መፍጠር፣ ማበረታታት አልፎ ተርፎም ተቀጣጣይ ቁሶችን ማምረትን የመሳሰሉ የጠላት ድርጊቶች አሁን ሙሉ በሙሉ ግልጽ ሆነዋል" ሲሉም አክለዋል።
የኢራንን ክስ ውድቅ የምታደርገው አሜሪካ ግን የቴህራን-ሞስኮ ግንኙነት ያሳስበኛል እያለች ነው።
በተለይም በዩክሬን ጦርነት ላይ የኢራን ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ ውለዋል መባላቸውን ተክተሎ አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን ያላቸውን ስጋት በመግለጽ ላይ ናቸው።
የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ እንደሚሉት ከሆነ ኢራናውያን ባለሙያዎች ዩክሬን በተቆጣጠራቻቸው የዩክሬን ክልልች ውስጥ እንዳሉና የዩክሬን መሰረተ ልማቶችን በማውደም ላይ ያሉትን የኢራን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ረገድ ለሞስኮ ጦር ከፍተኛ እርዳታ እያደረጉ ነው።
“ያንን ጥረት (ድሮኖችን ለማንቀሳቀስ) ለማገዝ አሁን በክራይሚያ መሬት ላይ ይገኛሉ”ም ነው ያሉት ጆን ኪርቢ።