የሩሲያን ጦር ምልክት በተሸከርካሪው ላይ የቀረጸው ጀርመናዊ በ4 ሺህ ዩሮ ተቀጣ
የሀምቡርግ ከተማ ነዋሪ የሆነው ይህ ግለሰብ የሩሲያን ጦር ደግፏል በሚል የገንዘብ ቅጣት ተጥሎበታል
የሩሲያ ጦር በዩክሬን ለልዩ ዘመቻ በሚል ወደ ዩክሬን ከገባ ስምንት ወር ሆኖታል
የሩሲያን ጦር ምልክት በተሸከርካሪው ላይ የቀረጸው ጀርመናዊ በ4 ሺህ ዩሮ ተቀጣ።
የጀርመኗ ሀምቡርግ ከተማ ነዋሪ የሆነ አንድ ግለሰብ የግሉ ተሸከርካሪ ላይ በነጭ ቀለም የሩሲያ ጦር ምልክት የሆነውን የዜድ ("Z") አርማ ቀርጿል ተብሏል።
ግለሰቡ ከስምንት ወራት በፊት ለልዩ ዘመቻ በሚል ወደ ዩክሬን ግዛት የገባውን የሩሲያ ጦር ደግፏል በሚል በሀምቡርግ ከተማ ፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶበታል።
ይህ ግለሰቡ ባሳለፍነው መጋቢት ወር ላይ በነጭ ወረቀት ላይ የዜድ ምልክትን በደማቁ በመጻፍ በአደባባዮች ሲያሽከረክር እንደነበርም ተገልጿል።
የግለሰቡ ተደጋጋሚ ድርጊት ሩሲያ በዩክሬን እየፈጸመች ያለውን ጦርነት ለመደገፍ ያደረገው ጥረት ነው ያለው የሀምቡርግ አቃቢ ህግ ለማስተማሪያነት በሚል ግለሰቡ 4 ሺህ ዮሮ እንዲከፍል ቅጣት እንደተጣለበት የጀርመን ድምጽ ዘግቧል።
ሩሲያ በዩክሬን እያደረገች ላለው ጦርነት የህዝብ ግንኙነት ስራ ለመስራት ወይም ድጋፍ ለማግኘት በሚል የጦር ተሸከርካሪዎቿ የዜድ ምስልን ተጠቅመው እንዲንቀሳቀሱ አድርጋለች።
በሞስኮ እና በተወሰኑ ሀገራት የዜድ ምስል የተጻፈባቸው ምልክቶች በአደባባዮች ላይ መታየት ጀምረውም የነበረ ሲሆን በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይም ለተወሰኑ ቀናት በስፋት ተሰራጭተዋል።
ጀርመን የትኛውም ዜጋዋ የሩሲያ ጦር ምልክት የሆነው ይህ የዜድ ምስልን በአደባባይ ይዞ መገኘት አልያም ማሰራጨት ዓለም አቀፍ ወረራን መደገፍ ስለሚሆን ድርጊቱን ከልክላለች።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ስምነተኛ ወሩ ላይ የሚገኝ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዩክሬናዊያን ወደ ጎረቤት ሀገራት ሲሰደዱ በቢሊዮን የሚቆጠር መሰረተ ልማት ደግሞ መውደሙን የተመድ ሪፖርት ያስረዳል።