ዘለንስኪ ሩሲያን አሸንፍበታለሁ ያሉትን "የድል እቅድ" ይዘው ወደ አሜሪካ አቀኑ
ዘለንስኪ ይህን ጉዞ ያደረጉት በአሜሪካ የዩክሬን ጦርነት ፖሊሲ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ነው
ዘለንስኪ እቅዱን ለአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና እሳቸውን ይተካሉ ተብለዉ ለሚጠበቁት ካማላ ሀሪስ እና ዶናልድ ትራምፕ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል
ዘለንስኪ ሩሲያን አሸንፍበታለሁ ያሉትን "የድል እቅድ" ይዘው ወደ አሜሪካ አቀኑ።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ስላዘጋጁት "የድል እቅድ" ለቅርብ አጋራቸው ለማስረዳት ወደ አሜሪካ አቅንተዋል።
ዘለንስኪ ይህን ጉዞ ያደረጉት በአሜሪካ የዩክሬን ጦርነት ፖሊሲ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
ዘለንስኪ በአሜሪካ ቆይታቸው እቅዱን ለአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና እሳቸውን ይተካሉ ተብለዉ ለሚጠበቁት ካማላ ሀሪስ እና ዶናልድ ትራምፕ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል። እቅዱ በምዕራባዊውያን የሚደገፍ ከሆነ የስነልቦናን ጨምሮ በሞስኮ ላይ ሰፊ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር፣ ፑቲን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ጦርነቱን እንዲያቆሙ ያስገድዳቸዋል ብለዋል ዘለንስኪ።
ዘለንስኪ ባለፈው አርብ እለት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "የድል እቅዱ ስትራቴጂካዊ አጋሮቻችን የሚወስዱትን ፈጣን እና ተጨባጭ እርምጃዎችን የያዘ ነው።"
ዘለንስኪ አክለውም እቅዱ ዩክሬን በዚህ አመት መጨረሻ ለምታዘጋጀው እና ሩሲያን ለመጋበዝ ለምትፈልግበት ለሁለተኛ ዩክሬን መር የሰላም ጉባኤ እንደ ድልድይ ሆኖ ያገልግል ብለዋል።
ይሁን እንጂ ሁለቱ አካላት የተራራቀ አቋም ነው ያላቸው።
ዘለንስኪ ዩክሬን የኔቶ እና የአውሮፓ ህብረት አባል እንድትሆን እና ሩሲያ ከዩክሬን ግዛት ሙሉ በሙሉ እንድትወጣ ይፈልጋሉ። ነገርግን ፑቲን የሰላም ንግግር የሚጀምረው ኪቪ በምስራቅ እና በደቡብ ከሚገኙት ቦታዎች ለቃ ስትወጣ እና የኔቶ አባል የመሆን ጥያቄዋን ስትተው ብለዋል።
ዘለንስኪ ይህን ጉዞ ያደረጉት ዩክሬን አጣብቂኝ ውስጥ በገባችበት ወቅት ነው። ትራምፕ በመጭው ጥቅምት ወር መጨረሻ የሚካሄደውን ምርጫ የሚያሰንፉ ከሆነ በዋናነት በአሜሪካ ወታደራዊ እና የፋይናንስ ድጋፍ ላይ ጥገኛ በሆነቸው ዩክሬን ላይ የፖሊስ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ።
ትራምፕ በቴለቪዥን በተካሄደ የምርጫ ክርክር ወቅት ዩክሬን ሩሲያን እንድታሸንፍ ይፈልጉ እንደሆነ ተጠይቀው ለመመለስ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ምርጫ የሚያሸንፉ ከሆነ ቢሮ ሳይገቡ ጦርነቱን ለማስቆም እንደሚሞክሩ ትራምፕ ተናግረዋል።
የዲሞክራት ፓርቲ ፕሬዝደንታዊ እጩ የሆኑት ካማላ ሀሪስ ትራምፕ ዩክሬን እንድትሸነፍ ይፈልጋሉ ሲሉ ከሰዋቸዋል።
የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን ባይደን የዘለንስኪን ጦርነቱን ለማሸነፍ ያስችላል የተባለውን እቅድ ለማየት መጓጓታቸውን ተናግረዋል።
ዘለንስኪ ይህ እቅድ የሚሳካው በባይደን ውሳኔ ነው ብለዋል።
ዩክሬን በግዛቷ ያለውን ኃይል ለመበተን አልማ በሩሲያ ክርስክ ግዛት ጥቃት ብትከፍትም፣ ሩሲያ ኃይሎች አሁንም ወደፊት እየገፉ ናቸው።