ጦሩ ለበጎ ፈቃደኛ ወታደሮች የሚከፍለው ገንዘብ በሀገሪቱ በተለያዩ ተቋማት በአማካኝ ከሚከፈለው ከአምስት እስከ ሰባት እጥፍ የሚበልጥ ነው
በዩክሬን ጦርነት በሩሲያ ወገን ሲዋጉ የነበሩ 70 ሺህ ወታደሮች መሞታቸው ተሰምቷል፡፡
በጦርነቱ ህይወታቸውን የሚያጡ ወታደሮች ፎቶ እና የህይወት ታሪካቸው በየቀኑ በሩሲያ መገናኛ ብዙሀን እና በማህበራዊ ትስስር ገጾች ይፋ ይደረጋል፡
ቢቢሲ አነዚህን መረጃዎች በማሰባሰብ እና የሟች ቤተሰቦችን በማነጋገር እንዲሁም መንግስት የሚወጣቸውን መረጃዎች በመከታተል ባዘጋጀው የመረጃ ትንተና 70 ሺህ 112 ወታደሮች መሞታቸውን ዘግቧል፡፡
ይህ ቁጥር ቢቢሲ ማረጋገጥ የቻላቸውን የወታደሮች ሞት ብቻ ያካተተበት ሲሆን የአጠቃላይ የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊጨምር እንደሚችል ጠቅሷል፡፡
ጦርነቱን ተከትሎ በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል የሚወጡ የሟቾች ቁጥር መረጃዎች ብዛት ትክክለኛ ያልሆኑ እና የተጋነኑ እንደሆኑ ይነገራል፡፡
የተለያዩ የምዕራባውያን የጥናት እና የደህንነት ተቋማት የሚያወጧቸውን መረጃዎች ደግሞ ሁለቱም ሀገራት አይቀበሏቸውም፡፡
ቢቢሲ አደረኩት ባለው የመረጃ ማሰባሰብ በ2022 በጦርነቱ ጅማሮ የሩሲያን ጦር በበጎ ፈቃድ የተቀላቀሉ ዜጎች ከአጠቃላይ የሞት መጠኑ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙ አመላክቷል፡፡
በዚህም ከሞቱት ወታደሮች መካከል 13 ሺህ ወይም 20 በመቶ በጎ ፈቃደኞች ሲሆኑ የእስር ጊዜያቸው እንደሚሻርላቸው ቃል ተገብቶላቸው ጦሩን የተቀላቀሉ ታሳሪዎች ደግሞ 19 በመቶ እንደሚሆኑ ተነግሯል፡፡
ካለፈው አመት ጥቅምት ወር ጀምሮ የበጎ ፈቃደኛ ወታደሮች ሳምንታዊ የሞት መጠን ከ100 ዝቅ ሳይል ቀጥሏል ፤ ይህ ቁጥር በአንዳንድ ሳምንታት እስከ 310 ከፍ ይላል፡፡
በሞቱ ወታደሮቿ ዙርያ በብዛት መረጃዎችን ይፋ የማታደርገው ዩክሬን በቅርቡ ባወጣችው መረጃ 31 ሺህ ወታደሮቿን በውግያው ማጣቷን ብታሳውቅም የአሜሪካ የደህንነት ተቋማት የሟቾች ቁጥር ከተጠቀሰው ጋር ሰፊ ልዩነት እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የሩሲያ ጦር በበጎ ፈቃደኝነት የሚቀላቀሉት አብዘሀኞቹ ዜጎች ከትናንሽ የሩስያ ከተሞች የመጡ የኢኮኖሚ ሁኔታቸውም ዝቅተኛ የሚባል እንደነበር የቢቢሲ ዘገባ አመላክቷል፡፡
በጦሩ ውስጥ የሚከፈላቸው ደመወዝ በሀገሪቱ በተለያዩ ተቋማት በአማካኝ ከሚከፈለው ከአምስት እስከ ሰባት እጥፍ እንደሚበልጥም ነው የተገለጸው፡፡
በርከት የሚሉት ጦሩን የሚቀላቀሉ በጎፈቃደኞች እድሚያቸው ከ42-50 ሲሆን ከሞቱት መካከል 250 የሚሆኑት እድሜያቸው ከ60 አመት በላይ ነው፡፡
ከኡዝቤኪስታን ፣ ማዕከላዊ እስያ እና ታጃኪስታን ለሩሲያ እየተዋጉ ህይወታቸው ካለፉ የውጭ ሀገራት ዜጎች መካከል ይጠቀሳሉ፡
ባለፈው አመቱ ሩሲያ ከኩባ ፣ ኢራቅ ፣ ሶርያ ፣ የመን እና ሰርቢያ ወታደሮችን ለመመልመል ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ ዘገባዎች መውጣታቸው ይታወሳል፡፡