የየመኑ ሁቲ አማጺ ቡድን በቀይ ባህር የሚወስደውን እርምጃ እንደሚገፋበት ገለጸ
አማጺ ቡድኑ ጥቃቱን የጀመረው ከፍልስጤማዊን ጎን መቆሙን ለማሳየት ነው ብሏል
በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማዊን ቁጥር 30 ሺህ አልፏል
የየመኑ ሁቲ አማጺ ቡድን በቀይ ባህር የሚወስደውን እርምጃ እንደሚገፋበት ገለጸ፡፡
ለፍልስጤም ነጻነት እታገላለሁ የሚለው ሐማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ የተጀመረው ጦርነት አምስት ወሩ ላይ ይገኛል፡፡
እስራኤል በወሰደችው የአየር እና ምድር ላይ ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማዊያን ቁጥር 30 ሺህ የደረሰ ሲሆን ጦርነቱ እንዲቆም ብዙዎች ቢጠይቁም እስካሁን ሊቆም አልቻለም፡፡
የየመኑ አማጺ ቡድን ከፍልስጤም ጎን ነኝ በሚል ከእስራኤል ፣አሜሪካ እና ብሪታንያ ጋር ንኪኪ የሆኑ የንግድ መርከቦችን በመምታት ላይ ይገኛል፡፡
የሁቲ አማጺያን በቀይ ባህር ላይ በሚያደርሰው ጥቃት ምክንያት የዓለም ንግድ በመጎዳት ላይ ሲሆን የግብጹ ስዊዝ ካናል መስመርም የሚያስተናግዳቸው መርከቦች ቁጥር በመቀነሱ ገቢውም ቀንሷል፡፡
አማጺ ቡድኑ በባብኤል ማንዲብ እና ኤደን ባህረ ሰላጤ የንግድ መስመር ላይ በሚመላለሱ መርከቦች ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት እንደሚቀጥልበት አስታውቋል ሲል አል አረቢያ ዘግቧል፡፡
የሁቲ አማጺ ቡድን መሪ አብዱል ማሊክ አል ሁቲ በተሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት በተላለፈ ንግግራቸው እንዳሉት የቀይ ባህር እና አረቢን ባህር ላይ እየተወሰደ ያለው ኦፕሬሽን ስኬታማ ነው ይህንንም እንቀጥልበታለን ብለዋል፡፡
የቀይ ባህር ትራንስፖርት ከዓለም ንግድ የ35 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን 12 በመቶ የሚሆነው የቀይ ባህር ትራንስፖርት በሁቲ አማጺያን ጥቃት ምክንት እንደተስተጓጎለ ተገልጿል፡፡
ግብጽ በበኩሏ ከስዊዝ ካናል ስታገኘው ከነበረው ገቡ የ50 በመቶ ቅናሽ እንዳሳየባት አስታውቃለች፡፡