የየመን ሁቲ አማጺያን ከፍልስጥማውያን ጋር ጎን መሆናችንን ለማሳየት ስንል መርከቡን መተናል ብለዋል
የየመን ሁቲ አማጺያን የብሪታንያ ነዳጅ ጫኝ መርከብ መምታታቸውን ገለጹ።
ከአራት ወራት በፊት የተጀመረው የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት አሁንም የቀተለ ሲሆን የጦርነቱ ተጽዕኖ እና ተሳታፊዎች እየጨመረ መጥቷል።
በተለይም አሜሪካ ለእስራኤል በቀጥታ ድጋፍ ማድረጓን ተከትሎ የጦርነቱ ተሳታፊዎች የጨመሩ ሲሆን የየመን ሁቲ አማጺያን ዋነኛ ተሳታፊ ሆነዋል።
የሁቲ አማጺያን እስራኤል በጋዛ የጀመረችውን ጦርነት ካላቋረጠች ጦርነቱን እንደሚቀላቀሉ አስቀድመው ባስጠነቀቁት መሰረት ከእስራኤል ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸው የንግድ መርከቦችን እየመቱ ይገኛሉ።
በዛሬው ዕለት ደግሞ በእስራኤል የሎጅስቲክስ ኩባንያዎች የሚንቀሳቀስ እቃ ጫኝ መርከብን በቀይ ባህር ትራንስፖርት መስመር ነዳጅ ጭኖ በመጓዝ ላይ እያለ በሚሳኤል መምታታቸውን አስታውቀዋል።
ንብረትነቱ የብሪታንያ የሆነው ይህ መርከብ ከእስራኤል ጋር ንኪኪ አለው በሚል በተፈጸመበት የሚሳኤል ጥቃት መቃጠሉን ሮይተርስ ዘግቧል።
የአሜሪካ እና ብሪታንያ ጦርም በሁቲ አማጺያን ይዞታዎች ላይ የአጸፋ እርምጃ ወስደዋል የተባለ ሲሆን በምዕራባዊ ሆዴዳህ ወደብ አቅራቢያ ባለ ቦታ ላይ የአየር ላይ ድብደባ ፈጽመዋልም ተብሏል።
አሜሪካ የቀይ ባህር ንግድ መስመርን ደህንነትን ለማስከበር በርካታ ሀገራትን ያሳተፈ ባህር ሀይል እያሳተፈች ቢሆንም ለአካባቢው ቅርብ የሆኑ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ራሳቸውን አግለዋል።
የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ራሳቸውን ያገለሉት ጥምረቱን ከመቀላቀላቸው በፊት እስራኤል በጋዛ የጀመረችውን ወታደራዊ ዘመቻ እንድታቆም ጠይቀዋል።
በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት የየመን አማጺ ሀይሎች ቻይና ቴህራንን በማግባባት ጣልቃ እንድትገባ ከአሜሪካ ጥያቄ ቀርቦላታል።
የኢራን ዋነኛ የንግድ አጋር የሆነችው ቻይና በጉዳዩ ላይ እስካሁን አስተያየት ከመስጠት ተቆጥባለች።