የሱዳን ጦር አዛዥ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከካርቱም ወጥተው የጦር ሰፈሮችን ጎበኙ
የጦር አዛዡ የሆኑት አል ቡርሃን የካቢኔ ስብሰባ ለማድረግም አቅደዋል ተብሏል
ጦሩ በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች የተያዙ በርካታ አካባቢዎችን ለመያዝ ከፈረንጆቹ ሚያዝያ 15 ጀምሮ እተየዋጋ ይገኛል
የሱዳን ጦር አዛዥ ጀነራል አልቡርሃን በሀገሪቱ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከባለፈው ሚያዝያ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከካርቱም ከተማ ወጥተው የተለያዩ የጦር ሰፈሮችን ጎብኝተዋል።
ሮይተርስ የመንግስት ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ አል ቡርሃን የክልላዊ የጦር ሰፈሮችን እና ፖርት ሱዳንን ከጎበኙ በኋላ ለንግግር ወደ ጎረቤት ሀገራት ያቀናሉ።
የጦር አዛዡ የሆኑት አል ቡርሃን የካቢኔ ስብሰባ ለማድረግም አቅደዋል ተብሏል።
ጦሩ በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች የተያዙ በርካታ አካባቢዎችን ለመያዝ ከፈረንጆቹ ሚያዝያ 15 ጀምሮ እተየዋጋ ይገኛል።
አልቡሃን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በትናንትናው እለት ከበነዋል ካሉት የጦሩ ዋና መቀመጫ በመውጣት በኦሞዱርማን ከተማ ሲንቀሳቀሱ በቪዲዮ ታይተዋል።
በተለቀቀው ቪዲዮ አል ቡርሃን በሰሜን ካርቱም የሚገኘውን የጦር መሳሪያ ማከማቻ ቦታ ጎብኝተዋል፤ ወታደሮችም ተሸክመዋቸው ደስታቸውን ሲገልጹ ነበር።
ጦሩ በምዕራብ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጋር በካርቱም፣ ኮርዶፋን እና ዳርፉር ግዛቶች እየተዋጋ ሲሆን ማዕከላዊ፣ ምስራቃዊ እና ሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍሎች የተረጋጉ እና በጦሩ ቁጥጥር ስር ያሉ ናቸው።
ሁለቱን ኃይሎች ለማስታረቅ የተደረጉ ሙከራች በሙሉ ውጤት አልባ ሆኗል። ችግሩን በሰላም ለመፍታት አዳጋች የሆነው ሁለቱም ተፋላሚዎች ጦርነቱን እናሸንፋለን የሚል ግምት በመያዛቸው ምክንያት መሆኑን ዲፕሎማቶች ይናገራሉ።
ተመድ ሁሉም የሀገሪቱን ክፍል ወደ ቀውስ እንዳይገባ አስጠንቅቋል።