ሩሲያ ከአጠቃላይ አመታዊ በጀቷ ከ32 በመቶ በላይ ለመከላከያ መደበች
የሀገሪቱ መንግስት ያቀረበው ረቂቅ በጀት በ2025 የሩሲያ ወታደራዊ በጀት 13.5 ትሪሊየን ሩብል እንዲሆን ጠይቋል
ሞስኮ ለመከላከያ ከፍተኛ ወጪ ከሚያወጡ ሀገራት መካከል ከአሜሪካ እና ቻይና በመቀጠል በ3ተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች
ሩሲያ ከአጠቃላይ አመታዊ በጀቷ ከ32 በመቶ በላይ ለመከላከያ መደበች።
ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ቀጥሎ በክብደቱ ተጠቃሽ ነው በሚባለው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ሁለቱም ሀገራት ከፍተኛ ሀብት እያፈሰሱ ይገኛሉ፡፡
የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ ጦርነቱ በኢኮኖሚ ላይ እያደረሰ የሚገኝውን ተጽዕኖ ለመቋቋም እና የዋጋ ንረቱን አሁን ከሚገኝበት 9.1 በመቶ በ2025 ወደ 4 በመቶ ዝቅ ለማድረግ የገንዘብ የወለድ ምጣኔ ወደ 19 በመቶ ከፍ አድርጓል፡፡
ዩክሬን ከምዕራባውያን አጋሮቿ በቢሊየን ዶላር የሚገመት የጦር መሳርያ ድጋፍ ስታገኝ ሞስኮ በበኩሏ በጦርነቱ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት በተከታታይ የመከላከያ በጀቷን በማሳደግ ላይ ትገኛለች፡፡
ወታደራዊ ተንታኞች የሩሲያ ጦር አሁን በሚገኝበት ሁኔታ ከዩክሬን የተሻለ የትጥቅ እና ወታደራዊ ቁመና እንዳለው ይመሰከሩለታል፡፡
ሆኖም ከጦርነቱ መራዘም ጋር በተያያዘ ግጭቱ የሚያስወጣው ገንዘብ እያደገ እንደሚገኝ ነው የሚገልጹት፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ሩሲያ ለ2025 በዐይነቱ ከፍተኛ ነው የተባለውን አዲስ የወታደራዊ በጀት ረቂቅ ማቅረቧ ተሰምቷል፡፡
በተያዘው አመት ለመከላከያ ከመደበችው በ28 በመቶ ብልጫ አለው በተባለው በጀት 13.5 ትሪሊየን ሩብል ወይም 145 ቢሊየን ዶላር እንዲሁን ለፓርላማዋ አቅርባለች፡፡
በ2024 ከተበጀተው ከ32 ቢሊየን ዶላር በላይ ጭማሪ የተደረገበት ይህ ከፍተኛ የመከላከያ በጀት በ2025 ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን ከአንድ አመት በኋላ በ2026 ዝቅ እንደሚደረግ በበጀት ረቂቁ ላይ ተገልጿል፡፡
በጀቱ ከመጽደቁ በፊት በሩሲያ በታችኛው እና የላይኛው ምክር ቤት መጽደቅ የሚኖርበት ሲሆን ቀጥሎም በፕሬዝዳንቱ ፊርማ ወደ ተግባራዊነት ይገባል፡፡
ዩክሬን በበኩሏ በመጪው ጥር ወር ሶስት አመቱን በሚደፍነው ጦርነት ውስጥ የመከላከል አቅሟን ለማሳደግ ከምዕራባውያን ተጨማሪ የጦር ማሳርያ ድጋፍ ይደረግላት ዘንድ ጥያቄዋን አጠናክራ ቀጥላለች፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሞስኮ የጦሯን አቅም ለማጠናቀር ተጨማሪ 180 ሺህ ወታደሮችን መከላከያዋን እንዲቀላቀሉ ለማድረግ እንቅስቃሴ ላይ ነች፡፡
ሶስተኛ አመቱን ሊደፍን የወራት እድሜ በቀሩት የዩክሬን ጦርነት የሩሲያ ጦር በምስራቃዊ ዩክሬን የሚያደርገውን ግስጋሴ ሲቀጥል ትላንት አዳሩን በ11 የዩክሬን ክልሎች ላይ መጠነ ሰፊ የተባለ የድሮን እና የሚሳኤል ጥቃት መፈጸሙ ተሰምቷል፡፡
ከ1000 በላይ ኢራን ሰራሾቹ ሻሂድ ድሮኖች ጥቅም ላይ በዋሉበት ጥቃት ከወራት በኋላ በአይነቱ ከፍተኛው ነው ተብሏል፡፡