ሩሲያ በዩክሬኗ ዶንባስ ክልል ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድ መጀመሯን አስታወቀች
ፕሬዝዳንት ፑቲን፤ “ሩሲያ ዩክሬንን የመውረር ፍላጎት የላትም፤ ከፊትለፊቷ የሚቆሙት ላይ ግን ከባድ ስርምጃ ትወስዳለች” ብለዋል
ዩክሬን በበኩሏ ሩሲያ ወረራ እየፈፀመችብኝ ነው ብላለች
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በየክሬኗ ምስራቅ ዶንባስ ክልል ለዩ ወታደራዊ ዘመቻ ማስጀመራቸው ተነግሯል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን በቴልቪዥን መስኮት በሰጡት መግለጫ፤ የወታደራዊ ዘመቻው ዋነኛ ዓላማ “ላለፉት 8 ዓመታት በኬይቭ በሚገኘው መንግስት የዘር ጭፍጨፋ ሲፈፀምባቸው የነበሩ ሰዎችን ነፃ ማውጣት ነው” ሲሉ አስታውቀዋል።
በሩሲያ ከሚደገፈው የአማጽያን ቡድን ጋር ጋር እየተዋጉ ያሉ የዩክሬን ወታሮች መሳሪያቸውን አስቀምጠው ወደቤታቸው እንዲመለሱም ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል።
“ሩሲያ ዩክሬንን የመውረር እቅድ የላትም” ያሉት ፕሬዚዳንት ፑቲን፤ ሆኖም ግን ሩሲያ ፊት የሚቆም ማንኛው ኃይል ካለ የሚሰጠው ምለሽ የከፋ ይሆናል ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ምንም እንኳ ሩሲያ “ወታደራዊ ዘመቻውን የጀመርኩት በዶንባስ ክልል ነው” ብትልም፤ በዩክሬኗ ዋና ከተማ ኬይቭ ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጾች መሰማታቸው ተነገሯል።
በኬይቭ የመጀመሪያው ፍንዳታ ከንጋቱ 11 ሰዓት ላይ የተሰማ ሲሆን፤ በመከታተልም አራት ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ከስፍራው የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በኬይቭ በሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያም ከፍተኛ ፍንዳታ እንዳለ የተነገረ ሲሆን፤ የተኩስ ድምጾች መሰማታቸውም ተነግሯል።
ዩክሬን በበኩሏ፤ “ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሙሉ በሙሉ ወረራ መፈጸም ጀምረዋል” በማለት ከሳለች።
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደምየትሮ ኩሌባ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ “በሰላማዊ የዩክሬን ከተማዎች ላይ ጥቃት እየተፈፀመ ነው” ብለዋል።
“ዩክሬን ራሷን ትከላከላለች፤ ታሸንፋለች ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ “ዓለም ፕሬዝዳንት ፑቲንን ሊያቆም ይገባል፤ ወደ ተግባር የሚገባበት ጊዜ አሁን ነው” ብለዋል።