በእንግሊዝ ማዕቀብ የተመቱት ሶስቱ ሩሲያዊ ቢሊየነሮች እነ ማን ናቸው?
ወሳኝ በሆኑ የሩሲያ የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች የጎላ ድርሻ እንዳላቸውም ነው የሚነገረው
ሶስቱም ቢሊየነሮች እያንዳንዳቸው ከ1 ቢሊዮን ዶላር የሚልቅ ሃብት አላቸው
የእንግሊሊ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ትናንት ማክሰኞ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ግንኙነት አላቸው ባሏቸው ሶስት ቢሊየነሮች እና ባንኮች ላይ ማዕቀብ መጣላቸውን አስታውቀዋል፡፡
ማዕቀቡ ሩሲያ በዶንባስክ ግዛት ለሚንቀሳቀሱ የሉሃንስክ እና የዶኔስክ ተገንጣይ የዩክሬን ታጣቂዎች እውቅና መስጠቷን እና በሰላም ማስከበር ስም ጦሯን ወደ አካባቢዎቹ ለማስገባት መወሰኗን ተከትሎ ነው የተጣለው፡፡
በእንግሊዝ ያላቸውን ሃብት እንዳያንቀሳቅሱ ለማድረግ ያስችላልም ተብሏል እገዳውን በተመለከተ በተሰጠ ማብራሪያ፡፡
ጆንሰን ሃብታቸውን እንዳያንቀሰቅሱ አገድኩ ያሏቸው ሶስት ሩሲያውያን ቱጃሮች ጌናዲ ቲምቼንኮ፣ ቦሪስ ሮተንበርግ እና ኢጎር ሮተንበርግ ይባላሉ፡፡
ጌናዲ ቲምቼንኮ እና ቦሪስ ሮተንበርግ በአሜሪካ ተመሳሳይ ማዕቀብ ከተጣለባቸው ከ8 ዓመታት በኋላ ነው ለዳግም ማዕቀብ የተዳረጉት፡፡
የቦሪስ ሮተንበርግ ወንድም ልጅ የሆነው ኢጎር ደግሞ ከ4 ዓመታት በኋላ በድጋሚ ለማዕቀብ ተዳርጓል፡፡
ለመሆኑ እንግሊዝ ሃብታቸውን እንዳያንቀሳቅሱ እንግሊዝ ያገደቻቸው እነዚህ ቱጃሮች እነ ማን ናቸው? ሃብታቸው ለምን እንዳያንቀሳቀስ ታገደስ?
ጌናዲ ቲምቼንኮ
የ69 ዓመት ጎልማሳ እና የፕሬዝዳንት ፑቲን የቅርብ ሰው ነው፡፡ የሮሲያ ባንክ ከፍተኛ የአክሲዮን ባለድርሻ ስለመሆኑ ይነገርለታል፡፡ ሮሲያ ባንክ ሩሲያ በፈረንጆቹ 2014 ክሬሚያን ከዩክሬንን ነጥቃ ስትጠቀልል አዳዲስ ቅርንጫፎችንና የኢንቨስትመንት ቢሮዎችን ከፍቶ ይንቀሳቀስ ነበረ፡፡ በክሬሚያ የተለያዩ የጉዞ እና የእንቅስቃሴ ካርዶችን ያትም ነበረ፡፡ ይህም ሩሲያ ክሬሚያን በደንብ ጠቅልላ ለመያዝ እንድትችል አግዟታል እንደ እንግሊዝ ባለስልጣናት ገለጻ፡፡
ቲምቼንኮ የሶስት ሃገራት ጥምር ዜጋ ነው፡፡ የሩሲያ፣ የፊንላንድ እና አርመን ዜግነትም አለው፡፡ በቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ ከሚገኝ የትምህር ተቋም በኤሌክትሪክ ምህንድስና በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቀ ሲሆን ከነዳጅና ጋዝ የሚነሳ ከፍተኛ ሃብትን ለማከማቸትና በቱጃርነት ለመጠቀስ በቅቷል፡፡ ፎርብስ የ23 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላሮች ባለቤት እንደሆነ በመጥቀስ ከቁንጮ የሩሲያ ቱጃሮች አንዱ ስለመሆኑ ያስቀምጣል፡፡
ገንቮር ከተሰኘ የነዳጅ ኩባንያ መስራች አባላት መካከል አንዱ ሲሆን በፈረንጆቹ 2014 በአሜሪካ ማዕቀብ ከመመታቱ አንድ ቀን በፊት በኩባንያው ያለውን የአክሲዮን ድርሻ ለቢዝነስ ሸሪኮቹ ሸጧል፡፡
የበረዶ ላይ ስፖርታዊ ጨዋታዎች አድናቂ ስለመሆኑ የሚነገርለት ቲምቼንኮ በፒተርስበርግ የራሱ ቡድን እንዳለው ይወሳል፡፡ ተንደላቆ የሚጓዝበት የራሱ ጄት ያለውም ሲሆን በባለቤቱ ስም የተሰየመችና ሌና የተሰኘች ቅንጡና ውድ መርከብ እንዳለችውም ይነገራል፡፡
ቦሪስ ሮተንበርግ
የ65 ዓመቱ አዛውንት የጂም እና የጁዶ ስፖርት አድናቂ ናቸው፡፡ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር አብረው ጂም ሰርተው ታግለውም ያውቃሉ፡፡ እንዲያውም ፑቲንን ቡጢ ገጣሚ ናቸው እየተባለም ይነገርላቸዋል፤ ፕሮፌሽናል የጁዶ አሰልጣኝ ስለመሆናቸው የሚነገርላቸው ቦሪስ ሮማኖቪች ሮተንበርግ፡፡ ለሃገራቸው በጁዶ የተለያዩ ሜዳሊያዎችን ማስገኘታቸውም ይወሳል፡፡
አዛውንቱ ከታላቅ ወንድማቸው አርኬዲ ሮማኖቪች ሮተንበርግ ጋር በመቀናጀት ከፈረንጆቹ 2001 ጀምሮ በምህጻረ ቃሉ ‘ኤስ.ኤም.ፒ’ የተሰኘ ዓለም አቀፍ ባንክ አቋቁመው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ‘ኤስ.ጂ.ኤም’ የሚባል የነዳጅ ማስተላለፊያ እና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢ ኩባንያም አላቸው፡፡
ፎርብስ የቦሪስ ሮማኖቪች ሮተንበርግን ጠቅላላ ሃብት 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ያደርሰዋል፡፡
የፕሬዝዳንት ፑቲን የቅርብ አጋርና የቢዝነስ ሸሪክ ናቸው የምትለው አሜሪካ የቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ኮንትራቶችን በተቋራጭ ስም ከፕሬዝዳንቱ ያገኛሉ ስትል ትከሳለች፤ ማዕቀብም ጥላለች፡፡
ኢጎር ሮተንበርግ
የ47 ዓመቱ ኢጎር የቱጃሩ አርኬዲ ሮማኖቪች ሮተንበርግ ልጅ ነው፡፡ አባቱ በአሜሪካ ማዕቀብ በተጣለበት ወቅት ተንቀሳቅሶ የተሻለ ሃብትን ለማካበት ችሏል፡፡ ሃብቱ በዋናነት ልክ እንደ አባቱ ሁሉ ከነዳጅና ኢነርጂ ሴክተር ከሚገኝ ገቢ የሚመነጭ ነው፡፡
‘ጋዝፕሮም ቡርኔ’ ከተሰኘው የአባቱ የነዳጅና ነዳጅ አሳሽ ኩባንያ የ79 በመቶ ድርሻ ማግኘቱም ከሩሲያ ቱጃር ኦሊጋርኮች ተርታ ስሙ እንዲጠቀስ አስችሎታል፡፡ አጎቱ ቦሪስ ሮማኖቪች ሮተንበርግንም በ‘ጋዝፕሮም ቡርኔ’ የ16 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ አለው፡፡
ጎልማሳው ኢጎር በሩሲያ የትራንስፖርት ዘርፍ የጎላ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ የሃሪቱ ቱጃሮች መካከልም አንዱ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የሃገሪቱ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎ ተቋም ከፍተኛ አመራርም ሆኖ ሰርቷል፡፡
ይህ የቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ ተወላጅ ባለ ትዳርና የሶስት ልጆች አባት ሲሆን በሞስኮ ተንደላቆ ይኖራል፡፡ ማዕቀቡ ሰለባ ካደረጋቸው ሶስቱ ቱጃሮች መካከልም ጎልማሳው ኢጎር ብቻ ነው፤ ሩሲያዊ ዜጋ የሆነው፡፡