ብሪታኒያ ሩሲያ አሁንም ዩክሬንን ልትወር እንደምትችል እያስጠነቀቀች ነው
“ምዕራባውያን ዩክሬንን ትወራለች”ብለው የሚጠብቋት ሩሲያ የምዕራባውያ የጦርነት ፕሮፖጋንዳ መክሸፉን አስታወቀች፡፡
ዛሬ ልምምድ ላይ ከነበሩት ወታደሮቿ የተወሰኑት መመለሳቸውን ይፋ ያደረገችው ሞስኮ ምዕራባውያን ጦርነትን እየጎሰሙ ቢሆንም ይህ ጦርነትን የመሻት ህልም “አንድም ጥይት ሳይተኮስ ከሽፏል” ብላለች፡፡ ሩሲያ ዛሬ ልምምድ ሲያደርጉ ከነበሩት ወታደሮቿ መካከል የተወሰኑት እንዲመለስ ማዘዟን ተከትሎ ከተለያየ የዓለም ክፍል አስተያየት እየተሰጠ ነው፡፡
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሜጀር ጄነራል ኢጎር ኮናሸንኮቭ የውጊያ ልምምዱ በመጠናቀቁ ወታደሮች ቀድሞ ወደነበሩበት ቋሚ ቦታቸው እንዲመለሱ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ ሩሲያ፤ ልምምድ ላይ የነበሩ ወታደሮችን እንዲመለሱ ውሳኔ ከማስተላለፏ ባለፈም ምዕራባውያን “ሞስኮ ዩክሬንን ልትወር ነው” የሚል ፕሮፖጋንዳ በተደጋጋሚ ቢያቀርቡም “ምንም ጥይት ሳይተኮስ ከሽፎባቸዋል” ብላለች፡፡
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ማሪያ ዛክሃሮቫ የዛሬው ዕለት የምዕራባውያን የጦርነት ፕሮፖጋንዳ “የከሸፈበት ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ቃል አቀባይ ማሪያ ዛክሃሮቫ የ”ምዕራባውያን ፕሮፖጋንዳ ምንም ጥይት ሳይተኮስ ውድቅ ሆኗል” ም ነው ያሉት፡፡
ቃል አቀባዩ የደቡብ እና ምዕራብ ወታደራዊ ግዛቶች የተሰጣቸውን ግዳጅ መጨረሳቸውን ገልጸው ቀድሞ ወደነበሩበት የጦር ሰፈር መመለስ እንደሚጀመር ይፋ አድርገዋል፡፡ ሩሲያ ይህንን ያደረገችው አሜሪካ እና ቭሪታኒያን ጨምሮ ሌሎችም ፤ሞስኮ ዩክሬንን ልትወር እንደሆነ እየከሰሱ ባለበት ወቅት ነው፡፡
የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን “ሩሲያ አሁንም ዩክሬንን ልትወር ትችላለች” የሚል ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ሩሲያ በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ የመስክ ሆስፒታሎችን እየገነባች እንደሆነ በመግለጽ ወረራው አሁንም ስጋታቸው እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ቦሪስ ጆንሰን አሁን” እያየን ያለነው የተደበላለቀ ሁኔታ” ነው ያሉ ሲሆን በአንድነት መቆም ይገባል ማለታቸውን ስካይ ኒውስ ዘግቧል፡፡ ሩሲያ ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ መጣል ላይ ቁርጠኛ እና አንድ መሆን ይገባል ማለታቸውም ተሰምቷል፡፡
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ከዲን ድርጅት (ኔቶ) ም ከብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ጋር የተቀራረበ አስተያየት ሰጥቷል፡፡ የኔቶ ዋና ጸሐፊ ጀንስ ስቶልተንበርግ በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል ያለው ውጥረት መቀነሱን የሚያመለክት ነገር እንደሌለ እየገለጹ ነው፡፡ ዋና ጸሐፊው ይህንን ያሉት የአባል ሀገራቱ የመከላከያ ሚኒስትሮች በቤልጀም ብራሰልስ በተሰባሰቡበት ወቅት ነው፡፡
አሜሪካ ፤ ሩሲያ በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ 130 ሺ ወታደሮችን አስጠግታ እንደነበር ስትገልጽ ቆይታለች፡፡