የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በትውልድ ከተማቸው የደረሰውን ጥቃቱን አውግዘዋል
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ የትውልድ ከተማ ክሪቪይ ሪህ በሩሲያ የሚሳይል ጥቃት መመታቷ ተነግሯል።
የክልሉ ገዥ ሰርሂ ሊሳክ እንዳሉት በጥቃቱ አራት ሰዎች በመኖሪያ ህንጻዎችና ስድስት ሰዎች ደግሞ በመጋዘን ውስጥ ተገድለዋል።
28 ሰዎች ደግሞ ቆስለው በሆስፒታሎች የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ነው።
ማክሰኞ ማለዳ ከደረሰው ጥቃት በኋላ ነዋሪዎቹ ከተቃጠለው አፓርትመንት ውጭ እያለቀሱ ነበር ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
በክሪቪይ ሪህ የተወለዱት የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በቴሌግራም ገጻቸው ጥቃቱን አውግዘዋል።
"የሩሲያ ገዳዮች በመኖሪያ ህንጻዎች፣ ተራ ከተሞች እና ሰዎች ላይ ጦርነታቸውን ቀጥለዋል" ብለዋል።
የዩክሬን ወታደራዊ እዝ የአየር መከላከያ ከ14ቱ ሚሳይሎች 10ሩን አወደምኩ ያለ ሲሆን ከአራት ኢራን ሰራሽ ድሮኖች ደግሞ አንዱን መትቶ መጣሉን ገልጿል።
ሩሲያ ስለ ጥቃቱ አስተያየት አልሰጠችም።
ሩሲያ በየካቲት 2022 ልዩ ተልዕኮ በሚል ጦርነቱን ከጀመረች በኋላ ሲቪሎችን ኢላማ ማደረጓን ብትክድም በዩክሬን ያሉ ከተሞችን ግን ደጋግሞ ደብድባለች።
ኬቭ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ እየጀመረች ባለበት ወቅት ሞስኮን በድንበር ተሻጋሪ ጥቃት ወንጅላለች።