የዩክሬን ጦር በባክሙት አቅራቢያ በሩሲያ ጦር ላይ አዲስ ድል ማግኘቱን ተናገረ
ኪየቭ የሩሲያ ኃይሎች መልሶ ማጥቃት እየሞከሩ ቢሆንም አልተሳካላቸውም ብላለች
በጦርነቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የጀርመንና የአሜሪካ የጦር ትጥቆች መታየታቸው ተነግሯል
መልሶ እያጠቃ ያለው የዩክሬን ኃይል በምስራቃዊቷ ባክሙት ከተማ አቅራቢያ በሚገኙት በርካታ የግንባሩ ክፍሎች ላይ ከኪሎ ሜትር በላይ መገስገሳቸውን የጦሩ ቃል አቀባይ አስታውቀዋል።
ግስጋሴው ሞስኮ ባለፈው ወር ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጠርኩ ባለችው በባክሙት አቅራቢያ ኪየቭ በዚህ ሳምንት አገኘሁት ያለችው ድል አካል ነው።
የምስራቅ ወታደራዊ እዝ ቃል አቀባይ ስለጉዳዩ ሲጠየቁ "በጠላት ላይ ጥቃት ለማድረስ እየሞከርን ነው። መልሶ ማጥቃትም አለብን። በባክሙት አቅራቢያ ውጊያ እስከ 1,400 ሜትር እርቀት በተለያዩ የግንባሩ ክፍሎች መራመድ ችለናል" ብለዋል።
- ሩሲያ የዩክሬን ጦር መሳሪያዎችን እንዳይታዘዙ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ መታጠቋ ተገለጸ
- የሩሲያ ጦር ኮማንደሮች በኒውክሌር ጦር መሳሪያ አጠቃቀም ላይ መምከራቸው ተገለጸ
ቃል አቀባይ ሰርሂ ቼሬቫቲ የሩሲያ ኃይሎችም መልሶ ማጥቃት እየሞከሩ ቢሆንም አልተሳካላቸውም ብለዋል።
የዩክሬን ጦር በአካባቢው የሩስያ ጦር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን እና ወታደራዊ መሳሪያዎችን እንዳወደመም ተናግረዋል።
ሮይተርስ የኪየቭን ግስጋሴና በጦር ሜዳ ያለውን ሁኔታ ማረጋገጥ አለመቻሉን ገልጿል።
ሞስኮ እና ኪየቭ ሁለቱም አርብ እለት በዩክሬን ከባድ ውጊያ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ የጀርመን እና የአሜሪካ የጦር ትጥቆች መታየታቸው የተነገረም ሲሆን፤ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው የዩክሬን የመልሶ ማጥቃት እርምጃ መጀመሩን ያሳያል ተብሏል።
ከዩክሬን በያዘችው ምስራቃዊ እና ደቡባዊ ክፍል ሰፊ ምሽግ የገነባችው ሩሲያ በበኩሏ በዚህ ሳምንት በኪየቭ የተደረገው ትልቅ ግፊት እንደከሸፈ ተናግራለች።