ሩሲያ በኦዴሳ ወደብ ጥቃት መሰንዘሯ ጥራጥሬ የመላክ የስምምንት ላይ "ከባድ ጥርጣሬ" የሚፈጥር ነው ተባለ
የዩክሬን ፐሬዝዳንት ሩሲያ በኦዴሳ ወደባ ላይ የሰነዘረችውን ጥቃት “አረመኔያዊ” ነው ሲሉ ኮንነውታል
ጥቀቱን ያወገዙት የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ “የእህል ስምምነቱን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው” ብለዋል
ሩሲያና ዩክሬን ጥራጥሬ ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ ከተስማሙ ከሰዓታት በኋላ ሩሲያ በዩክሬኑ ኦዴሳ ወደብ ላይ ጥቃት መሰረንዟ ተሰምቷል።
ሩሲያ በኦዴሳ ወደብ ላይ ያደረሰችውን ጥቃት ለተደረሰው ስምምነት ያለት ቁርጠኝነት ላይ "ከባድ ጥርጣሬ" የሚፈጥር ነው ተብሏል።
ጥቃቱ በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል የዩክሬይንን የእህል ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ታሪካዊ ስምምነት ከተደረሰ ከሰዓታት በኋላ የተሰነዘረ እንደመሆኑ በበርካቶች ዘነድ ስምምነቱ ላይሳካ ይችላል የሚል ስጋት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።
ሞስኮ በጥቃቱ ዙሪያ የተናገረችው ነገር የለም። ጥቃቱ ቢሰነዘርም ኪዬቭ ለገበያ የሚቀርበውን እህል ለመላክ ዝግጅቷን እንደቀጠለች ነው።
ጥቃቱን በተመለከተ በሩሲያ በኩል እስካሁን የተባለ ነገር ባይኖርም፤ ዘለንሰኪ ግን ጥቃቱ ሞስኮ ስምምነቱን ስለማክበሯ እንደማትታመን የሚያሳይ መሆኑ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ፤ ሩሲያ በኦዴሳ ወደብ ላይ ያደረሰችውን ጥቃት “አረመኔያዊ” ነው ሲሉም መግለጻቸውም ፍራንስ-24 ዘግቧል።
ጥቃቱን ከዩክሬን በተጨማሪ በርካቶች አውግዘውታል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ሩሲያ የዓለም የምግብ ቀውስን እያባባሰች ነው ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሂፍ ከሰዋል፡፡
ጥቃቱ ሩሲያ በስምምነቱ ላይ ባላት የቁርጠኝነት ተአማኒነት ላይ "ከባድ ጥርጣሬን ይፈጥራል"ም ብለዋል።
ሩሲያ ጥቃቷን ማቆም እና የተስማማችበትን የእህል ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ አለባት" ሲሉም ነው ያሳሰቡት ብሊንከን።
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሃላፊ ጆሴፕ ቦሬል በኦዴሳ ወደብ የተፈጸመው ጥቃት ሩሲያ ለዓለም አቀፍ ህግ ችላ ማለቷን ያሳያል ሲሉ ተደምጠዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝም እንዲሁ ጥቃቱን ያወገዙ ሲሆን፤ “የእህል ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው” ብለዋል።
በቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አማካኝነት፤ በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል የተደረሰው የእህል ምርትን ወደ ውጭ የመላክ ስምምነት መደረሱ የሚታወስ ነው፡፡
በዚህ ስምምነት በተለይም በእህል ምርት እጥረት ኩፉኛ የተጎዱት አፍሪካውያን ደስታቸው እንደገለጹ አይዘነጋም፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሀማት ስምምነቱ የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀ መንብር ማኪ ሳል በወርሃ የካቲት ወደ ሩሲያ አቅንተው በጉዳዩ ላይ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ያደረጉት ምክክር ፍሬያማ መሆኑ የሚያመላክት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ማኪ ሳል ከወራት በፊት ወደ ሩሲያ ባደረጉት ጉዞ ፕሬዝዳንት ፑቲንን አግኘተው የሩሲያ-የክሬን ጦርነት አፍሪካ ላይ የፈጠረው ተጽዕኖ ቀላል እንዳልሆነ ማስረዳታቸው አይዘነጋም፡፡
ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ለሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን “ምንም እንኳን የአፍሪካ ሀገራት ከግጭቱ ስፍራ ርቀው ቢገኙም፣ ጦርነቱ ባስከተለው የምጣኔ ሀብት ተጽእኖ ሰለባ ሆነዋል” ማለታቸው ይታወሳል፡፡
በዚህም የምግብ አቅርቦቶች ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ ከጣሉት ማዕቀብ “ውጪ” መሆን እንዳለባቸው ነበር ማኪ ሳል ፑቲንን የጠየቁት፡፡
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከፕሬዝዳንት በበኩላቸው፣ ሩሲያ “ሁልጊዜም ከአፍሪካ ጎን ናት”የሚል ጥቅል የሚመስል ግን ደግሞ አውንታዊ ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
ያም ሆኖ አፍሪካን ጨምሮ የዓለም የምርት ችግርን ያቃልላል የተባለለት ስምምነት በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል መፈረሙ በአፍሪካ ህብረት በኩል የሚበረታታ እርምጃ ነው ተብሎለታል፡፡ ስምምነቱ የዩክሬን ጥቁር ባህር ወደቦች የግብርና ምርቶችን ለመላክ የሚያስችል አስደናቂ ስምምነት መሆኑም እየተነገረ ነው።