የዩክሬን ጦርነት የምዕራባዊያን የበላይነት እያበቃ ለመሆኑ ማሳያ መሆኑን ቶኒ ብሌር ተናገሩ
ጦርነቱ ቻይና ዓለምን እንደምትቆጣጠር ማሳያ እንደሆነም የቀድሞው የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ተናግረዋል
ዓለማችን በቀጣይ በሁለት ወይም ሶስት ልዕለ ሀያላን ሀገራት የመመራት እድሏ ከፍተኛ ነው ተብሏል
የዩክሬን ጦርነት የምዕራባዊያን የበላይነት እያበቃ ለመሆኑ ማሳያ መሆኑን ቶኒ ብሌር ተናገሩ፡፡
የቀድሞው የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር እንዳሉት የዩክሬን ጦርነት የምዕራባዊያን የበላይነት እያበቃ መምጣቱን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ጦርነቱ የምዕራባዊያን የበላይነት እያበቃ መሆኑን እና የቻይና ተጽዕኖ እያደገ ለመምጣቱ ማሳያ መሆኑንም ብሌር በለንደን በተዘጋጀ ሴሚናር ላይ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ምዕራባዊያን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከሶቪየት ህብረት ጋር ተጋርጦባቸው የነበረውን የበላይነት ማሸነፍ ቢችሉም አሁን ግን በታሪካዊ እጥፋት ላይ መሆናቸውን ብሌር አክለዋል፡፡
አሁን የምዕራባዊያን የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ የበላይነት መጨረሻ ላይ እንገኛለን ያሉት ብሌር ዓለም በቀጣይ ቢያንስ በሁለት ወይም ከዚያ በላይ ባሉ ልዕለ ሀያላን ሀገራት እጅ ስር መውደቋ አይቀርም ብለዋል፡፡
ይህም ዓለማችን በሩሲያ ሳይሆን በቻይና የበላይነት ልትምራ እንደምትችልም ቶኒ ብሌር በሴሚናሩ ላይ ተናግረዋል ተብሏል፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦርን ወይም ኔቶን በአባልነት እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት ካመሩ 145ኛ ቀናቸው ላይ ያሉ ሲሆን ከ15 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለዋል፡፡
በአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት የሚመራው የምዕራባዊያን ቡድን ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ከመርዳት ጀምሮ ከ6 ሺህ በላይ ማዕቀቦችን በሩሲያ ላይ ጥለዋል፡፡
ሩሲያ በበኩሏ ሰፊ ሸማች ካላቸው ቻይና እና ህንድ ጋር ንግዷን በማሳደግ ላይ ስትሆን በተለይ የቻይና ድጋፍ ከፍተኛ እንደሆነ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡