ሩሲያ ጾታ መቀየርን የሚፈቅዱ ሀገራት ዜጎቿን በጉዲፈቻ እንዳይወስዱ ከለከለች
ሩሲያ እንደ አሜሪካ ያሉ ህጻናት ተፈጥሯዊ ጾታቸውን እንዲቀይሩ በሚፈቅዱ ሀገራት ላይ ጉዲፈቻን የሚከለክል ነባር ህግ አላት
አዲሱ ህግ ህጻናትን ለጾታዊ ጉዳት የሚዳርጉ ጉዳቶችን ለማስቀረት ያለመ ነው ተብሏል
ሩሲያ ጾታ መቀየርን የሚፈቅዱ ሀገራት ዜጎቿን በጉዲፈቻ እንዳይወስዱ ከለከለች።
በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከምዕራባዊያን ሀገራት ጋር ሆድና ጀርባ የሆነችው ሩሲያ አዲስ የጉዲፈቻ ህግ አዘጋጅታለች።
አዲሱ ህግ ህጻናት በተፈጥሯቸው ካገኙት ጾታ ውጪ በሰው ሰራሽ መልኩ ጾታቸውን እንዲቀይሩ የሚፈቅድ ህግ ያላቸው ሀገራት ህጻናትን በማደጎ አልያም በጉዲፈቻ እንዳይወስዱ የሚከለክል ነው።
ዱማ የሚባለው የሩሲያ ህግ አውጪ ምክር ቤት ሩሲያዊያን ህጻናትን በማደጎ ለመውሰድ የሚፈልጉ የውጭ ሀገራት ዜጎች የግድ በሀገራቸው ጾታ መቀየርን የሚከለክል ህግ እንዲኖራቸው ያስገድዳል።
የሩሲያ ፓርላም ይህን ህግ ያዘጋጀው ህጻናትን ከተለያዩ ጾታዊ ጥቃቶች ለመጠበቅ በሚል እንደሆነ ተገልጿል።
ሩሲያ ከዚህ በፊት ሰዎች በይፋ ተፈጥሯዊ ጾታቸውን እንዲቀይሩ የሚፈቅድ ህግ ያላቸው እንደ አሜሪካ ያሉ ሀገራት ሩሲያዊያን ህጻናትን በማደጎ እንዳይወዱ ከልክላ ነበር።
አዲስ የተዘጋጀው ህግ 397 ድጋፍ እና በአንድ ተቃውሞ አስገዳጅ ህግ ሆኖ እንዲጸድቅ ወደ ሚቀጥለው ደረጃ እንዲተላለፍ ተወስኗል።
የሩሲያ ህግ አውጪ ምክር ቤት ሊቀመንበር ቪያስችላቭ ቮሎዲን እንዳሉት ህጻናት በማደጎ ተላልፈው ከተሰጡ በኋላ ተገደው አልያም በሌሎች ጫናዎች ምክንያት ጾታቸውን እንዲቀይሩ እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ሩሲያ በዓለማችን ብዙ ህጻናት በማደጎ ከሚወሰድባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት።
እንዲሁም ሀገሪቱ የማህጸን ኪራይ ህግን የምትፈቅድ ሲሆን ከተለያዩ ሀገራት ዜጎች በመምጣት ህጻናቱ ከተወለዱ በኋላ በተለያዩ መንገዶች ይወሰዳሉ።