የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ዋግነር አሁን ላይ እየተንቀሳቀሰ ያለው በአፍሪካ እና የሩሲያ አጋር በሆነችው ቤላሩስ ውስጥ ብቻ መሆኑን ገልጿል
የሩሲያው ተዋጊ ቡድን ዋግነር በዩክሬን እየተዋጋ አለመሆኑን ገለጸ።
የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ዋግነር አሁን ላይ እየተንቀሳቀሰ ያለው በአፍሪካ እና የሩሲያ አጋር በሆነችው ቤላሩስ ውስጥ ብቻ መሆኑን እና ወታደሮቹ በዩክሬን ውጊያ እየተሳተፉ አለመሆናቸውን ገልጿል።
ዩክሬን በትናንትናው ቤላሩስ ወደ ድንበር ያስጠጋቻቸውን ብዙ ቁጥር ያላቸው ወታደሮች ወደ ኋላ እንድትመልስ ጥሪ አቅርባለች።
ዩክሬን እንደገለጸችው ከሆነ ወደ ድንበር ከተጠጉት የቤላሩስ ወታደሮች ውስጥ የቤላሩስ ልዩ ኃይሎች እና የቀድሞ የዋግነር ቅጥረኛ ተዋጊዎች ይገኙበታል።
ዋግነር ባልተለመደ መልኩ ባወጣው መግለጫ ሰራተኞቹ በአፍሪካ እና በቤላሩስ ብቻ እንደተሰማሩ አስታውቋል።
"በሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ውስጥ ወይም በሌላ ቦታ የኩባንያው(ዋግነር) አካል የለም" ብሏል ዋግነር።
መግለጫው ዋግነር "አሁን በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ ውስጥ እየተሳተፈ አይደለም" ብሏል። ሮይተርስ የእዚህን መረጃ ትክክለኛነት ማረጋገጥ እንደማይችል ገልጿል።
"ሁኔታዎች የሚለወጡ ከሆነ እናሳውቃለን" ብሏል ዋግነር።ዋግነር በአፍሪካ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ምዕራባውያን አስግቷቸዋል።
ዋግነር በዩክሬኑ ጦርነት በከሩሲያ ኃይሎች ጎን በመሰለፍ በተለይም ከረጅም እና ከከባድ ጦርነት በኋላ በፈረንጆቹ ግንቦት 2023 ወሳኝ የተባለችውን የባክሙት ከተማን ተቆጣጥሮ ለሩሲያ ጦር ማስረከቡ ይታወሳል።
በሚቀጥለው ወር የዋግነር መሪ የሆነው የቭጀኒ ፕሪጎዥን በሩሲያ መከላከያ ኃይል ላይ ለአጭር ጊዜ የቆየ አመጽ አካሂዶ ነበር። አመጹን ተከትሎ በቤላሩስ አደራዳሪነት መሪው ፕሪጎዥን እና ጦሩ ወደ ቤላሩስ እንዲጠለሉ ከክሬሚሊን ጋር ስምምነት ላይ ተደረሰ።
በፈረንጆቹ ነሐሴ 2023 ፕሪጎዥን እና ሌሎች የዋግነር ከፍተኛ አመራሮች ሩሲያ ውስጥ በአውሮፕላን መከስከስ አደጋ ህይወታቸው አለፈ።