ሶስተኛው የዓለም ጦርነት ከተጀመረ በአውሮፓ ብቻ እንደማይወሰን ሩሲያ አስጠነቀቀች
ምዕራባዊያን ሀገራት ለዩክሬን እያደረጉት ያለው ድጋፍ ለሶስተኛው የዓለም ጦርነት መነሻ ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል
ዩክሬን በበኩሏ የኩርስክ ጥቃት የሩሲያ ዛቻ ባዶ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብላለች
ሶስተኛው የዓለም ጦርነት ከተጀመረ በአውሮፓ ብቻ እንደማይወሰን ሩሲያ አስጠነቀቀች፡፡
ሶስተኛ ዓመቱ ላይ የሚገኘው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት መልኩን እየቀያየረ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡
ከ20 ቀን በፊት ዩክሬን ምዕራብ ሩሲያ በኩል ባለችው ኩርስክ ግዛት በኩል ያልተጠበቀ ጥቃት በማድረስ በርካታ መንደሮችን መቆጣጠሯ ይታወሳል፡፡
ሩሲያ ጥቃቱ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በውጭ ሀይሎች ላይ የተፈጸመባት ጥቃት መሆኑን አስታውቃለች፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከጥቃቱ ጀርባ ምዕራባዊያን ሀገራት ሰራሽ የሆኑ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች እንዳሉ ይፋ አድርጋለች፡፡
ድምጹ ብቻ የሚያሸብረው የሩሲያው “ቲዩ-95” ቦምብ ጣይ አውሮፕላን
የሩሲያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጊ ላቭሮቭ በሞስኮ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳሉት የዩክሬን ኩርስክ ጥቃት የሶተኛው የዓለም ጦርነትን የሚቀሰቅስ ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም “ምዕራባዊያን ለዩክሬን በሰጡት መሳሪያ ሩሲያን እንድትመታ በማድረግ በእሳት እየተጫወቱ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“ሶስተኛው የዓለም ጦርነት ከተጀመረ በአውሮፓ ብቻ የሚያበቃ አይደለም” ያሉት ሚኒስትሩ ምዕራባዊያን ዩክሬን በመጠቀም ወደ ከፋ ውድመት እየመሩ ነው ሲሉም አስጠንቅቀዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬን በኩርስክ ለፈጸመችው ጥቃት ተገቢው ምላሽ ይሰጣል ማለታቸው ይታወሳል፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው ከኩርስክ ጥቃት በኋላ በሰጡት መግለጫ የሩሲያ ያ ሁሉ ዛቻ ምንም ነው ሲሉ ተናግረው ምዕራባዊን ሀገራት ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
እንደ ሩሲያ ዕምነት ከሆነ ዩክሬን በሩሲያዋ ኩርስክ ግዛት ጥቃት የፈጸመችው በምዕራባዊን ሀገራት ጦር መሳሪያ፣ የሳተላይት መረጃዎች እና ሌሎች ድጋፎች ታግዛ ነው፡፡
ሩሲያ ከ2022 ጀምሮ ሉዓላዊ ደህንነቷ አደጋ ውስጥ ከገባ የኑክሌር ጦር መሳሪያዋን እንድትጠቀም የሚፈቅድላት ህግ እንዳላት ፕሬዝዳንት ፑቲን በተደጋጋሚ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል፡፡