ብሪታንያ፣ ኖርዌይ፣ ዩክሬን እና ሌሎች ሀገራት በሩሲያ እንዳይጓዙ የታገዱ ሀገራት ናቸው
ሩሲያ ወዳጅ አይደሉም ያለቻቸውን ሀገራት በግዟቷ እንዳይጓዙ አገደች።
ሩሲያ ወደ ዩክሬን ግዛት ለልዩ ዘመቻ በሚል ተልዕኮ ከላከች እና ከዩክሬን ጋር የቀጥታ ጦርነት ከገጠሙበት ጊዜ ጀምሮ በሞስኮ ላይ ከስድስት ሺህ በላይ ማዕቀቦች ተጥለዋል።
ሩሲያም ማዕቀብ በጣሉባት በአሜሪካ እና ሌሎች የምዕራባዊያን ሀገራት ላይ የአጸፋ እርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች።
በሩሲያ ከተወሰዱ ማዕቀቦች መካከልም የሞስኮ ወዳጅ አይደሉም ካለቻቸው ሀገራት ጋር በሩብል መገበያየት፣ የነዳጅ ንግዶችን መቀነስ፣ ማዕቀብ መጣል እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።
ምዕራባዊያን ሀገራት በሩሲያ ላይ ማዕቀባቸውን የቀጠሉ ሲሆን፤ በተለየም በህዝበ ውሳኔ በዩክሬን ስር የነበሩ አራት ግዛቶችን ወደ ሩሲያ ከቀላቀለች ጀምሮ ማዕቀቦች እየተጣሉባት ይገኛሉ።
ለዚህ ማዕቀብም ምላሽ የሚሆን ወዳጅ አይደሉም በተባሉ ሀገራት ላይ የጉዞ እገዳ መጣሏን ሩሲያ አስታውቃለች።
ብሪታንያ፣ ኖርዌይ፣ ዩክሬን እና ሌሎችም ሀገራት በሩሲያ የጉዞ እገዳ የተጣለባቸው ሀገራት ሲሆኑ እነዚህ ሀገራት በሩሲያ ግዛት ውስጥ የጭነት አገልግሎት እንዳያደርጉ መከልከላቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ዩክሬን ክሪሚያን ከተቀረው የሩሲያ አካባቢዎች የሚያስተሳስረው ዋና ድልድይ ላይ ባሳለፍነው ቅዳሜ ጉዳት ማድረሷን ተከትሎ ሞስኮ በትናንትናው ዕለት ከ80 በላይ የሚሳኤል ጥቃቶችን አድርሳለች።
በዚህ የሚሳኤል ጥቃት የዩክሬን ዋና ዋና ከተሞች የተጎዱ ሲሆን ወታደራዊ ተቋማት እና የሀይል መሰረተ ልማቶች ከአገልግሎት ውጪ ሆነዋል።
የሩሲያን ጥቃት አሜሪካንን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ያወገዙ ሲሆን ለዩክሬን ተጨማሪ የጦር መሳሪያ ድጋፎች እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።