ሩሲያ “ወዳጅ አይደሉም”ያለቻቸውን 48 ሃገራት ዝርዝር ይፋ አደረገች
ፕሬዝዳንት ፑቲን “ወዳጅ አይደሉም” ከተባሉት ሃገራት የተገኘ ብድር በሩሲያ ገንዘብ (ሩብል) እንዲመለስ አዘዋል
ሃገራቱ ከዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ በሩሲያ ላይ ማዕቀብን ጨምሮ የተለያዩ እገዳዎችን የጣሉና እርምጃውን የደገፉ ናቸው
ሩሲያ በወሰዱባት እርምጃ “ወዳጅ አይደሉም”ያለቻቸውን 48 ሃገራት ዝርዝር ይፋ አደረገች፡፡
ሃገራቱ ከዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ በሩሲያ እንዲሁም በተቋማቶቿ እና ባለሃብቶቿ ላይ ማዕቀብን ጨምሮ የተለያዩ እገዳዎችን የጣሉ እርምጃዎቹን የደገፉ ናቸው፡፡
ያልተገቡ ጸብ አጫሪ እርምጃዎችን በሩሲያ ላይ ወስደዋል የተባሉት እነዚህ ሃገራት እርምጃዎቹን የተመለከተ የአጸፋ እርምጃ አዋጅ ባወጡት በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ትዕዛዝ ነው በ2 ቀናት ውስጥ ተዘርዝረው ይፋ ይሆኑት፡፡
ዛሬ ሰኞ ይፋ በሆነው ዝርዝር መሰረትም ዩክሬንን፣ አሜሪካን፣ ካናዳን እና የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራትን ጨምሮ 48 ሃገራት ወዳጅ እንዳይደሉ ተዘርዝሮ ይፋ ሆኗል፡፡
በዋናነት ምዕራባዊ የሚባሉትን ሃገራት የሚመለከት ነው የተባለለት ዝርዝሩ ጃፓንን፣ ደቡብ ኮሪያን፣ አውስትራሊያን፣ ኒውዚላንድን፣ ኖርዌይን፣ ሲንጋፖርን እንዲሁም ታይዋንን ያካትታል፡፡
የዩናይትድ ኪንግደም አካል የሆኑ የጀርሲ፣ አንግላ፣ ብሪቲሽ ቨርጂን አይስላንድስንና ጂብራልታርን እንዲሁም ራስ ገዟን የፈረንሳይ ግዛት ሞናኮን ያካትታል፡፡
ሞንቴኔግሮ፣ ስዊዘርላንድ፣ አልባኒያ፣ አንዶራ፣ አይስላንድንና ሌይቼንስቴይንንም ያካትታል፡፡
በፕሬዝዳንት ፑቲን ፊርማ በጸደቀው አዋጅ ተዘርዝረው ይፋ ከሆኑት ሃገራትና ተቋማት የተበደሩ የሩሲያ ተቋማትና ባለሃብቶች ብድራቸውን በሩሲያ ገንዘብ (ሩብል) እንዲከፍሉ የሚያስገድድም ነው፡፡
ለዚህም ተበዳሪዎቹ የሃገሪቱን ማዕከላዊ ባንክ ፈቃድ ማግኘት፣ አበዳሪዎቹ ደግሞ በባንኩ የሩብል አካውንት መክፈት አለባቸው ተብሏል፡፡
ሆኖም አዋጁ ከ10 ሚሊዮን ሩብል የበለጠ ወይም ተመጣጣኝ የምንዛሬ መጠን ያለውን ብድር የሚከፍሉ ተቋማትንና ኩባንያዎችን የሚመለከት ነው፡፡
አሜሪካንና ምዕራባዊ አጋሮቿን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ ሃገራት በሩሲያ ላይ ከዓለም የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች ማገድን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዳቸው ይታወሳል፡፡