ሩሲያ፤ ሀገራት ሲደግፉም ሆነ ሲቃወሙ የውጭ ጫናዎች እንዳለባቸው “እረዳለሁ” አለች
ሞስኮ፤ ለነዳጅና ለስንዴ ምርቶች መወደድ ተጠያቂዎቹ “አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት ናቸው” ብላለች
ሩሲያ በዓለም መድረኮች ላይ “ድጋፍ ስጡኝ” ብላ እንደማትለማመጥም ተገልጿል
ሩሲያ፤ በተባበሩት መንግስታት ድርጀት ስብሰባዎችና በሌሎች ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች ላይ ሀገራት በድጋፍም ሆነ በተቃውሞ ጎራ ሲሆኑ የውጭ ጫናዎች እንዳሉባቸው ገለጸች።
በኬንያ የሩሲያ አምባሳደር ከሰሞኑ በሁለቱ ሀገራት ግንኙነትና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ቃለ ምልልስ አድርገዋል።አምባሳደር ዲሚትሪ ማክሲሞኤቭ ቆይታ ያደረጉት በኬንያ ከሚታተመው ዕለታዊው ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ ጋር ነበር።
ዲፕሎማቱ፤ ኬንያ ከአሜሪካና ከምዕራብ ወገን መቆሟና ከሩሲያ ተቃራኒ አቋም ማራመዷን ተከትሎ ለተነሳላቸው ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል።
አምባሳደር ዲሚትሪ ማክሲሞኤቭ ሀገራት ሉዓላዊ በመሆናቸው የፈለጉትን አቋም የማራመድ፣ የመደግፋና የመቃወም መብት እንዳላቸው ሀገራቸው እንደምትገነዘብ ተናግረዋል።
አምባሳደሩ፤ ሀገራቸው ከኬንያ ጋር ያላት ትብብር እያደገና እየተለወጠ ነው ያሉ ሲሆን፤ በ2009 ቭላድሚር ፑቲን እና የኬንያ አቻቸው ኡሁሩ ኬንያታ በሶቺ ከተማ በተካሄደው የአፍሪካ ሩሲያ ጉባዔ ላይ በአካል መገናኘታቸውን ለአብነት አንስተዋል።
አምባሳደሩ እንዳሉት ሩሲያ የተመድ አባል ሀገራት ድጋፍ እንዲሰጧት ለማድረግ ልመና ውስጥ አትገባም ብለዋል። ሀገራትም በተመድ ስብሰባዎች ላይ የፈለጉትን የመደገፍና የመንቀፍ አሊያም ድምጽ ያለመስጠት መብታቸውን ሩሲያ ታከብራለችም ብለዋል።
ምንም እንኳን ምዕራቡ ዓለም ሩሲያ “ወረራ እየፈጸመች ነው” ቢልም ሩሲያ ግን “ወታደራዊ ተልዕኮ” እያደረገች ስለመሆኑ እየገለጸች ነው።
በኬንያ ያሉት የሩሲያ ዲፕሎማትም ሩሲያ ወረራ እያደረገች እንዳልሆነ ይልቁንም ከአራት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑና በዩክሬን የሚገኙ ሩስኪ ቋንቋ የሚናገሩ ዜጎችን ለመታደግ የተጀመረ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ኬንያ ደግሞ በዓለም ላይ ለተከሰተው የዋጋ ንረት ተጠያቂ ማድረግ ያለባት አሜሪካንና የአውሮፓ ህብረት እንደሆነም አምባሳደሩ ተናግረዋል።
ለድንጋይ ክሰል፣ ለነዳጅና ለስንዴ ምርቶች መወደድ ማን ተጠያቂ መሆን እንዳለበት መገንዘብ እንደሚገባ ያነሱት የሩሲያው ድፕሎማት የዚህ ተጠያቂዎች እነማን እንደሆኑ ግልጽ ነው ብለዋል።