በዩክሬን ድንበር የተደረደሩ የሩስያ የጦር አውሮፕላኖች ምን እየተጠባበቁ ነው?
የሳተላይት ምስሎች 13 የሩስያ አውሮፕላኖች ከዩክሬን ድንበር በ500 ማይል ርቀት ላይ እንደሚገኙ ያሳያሉ
ይህም ሞስኮ በኬቭ ላይ መጠነ ሰፊ የአየር ድብደባዎችን ለመፈጸም መዘጋጀቷን ያሳያል እየተባለ ነው
ሩስያ በዩክሬን ላይ “መጠነ ሰፊ” የአየር ጥቃት ለመፈጸም ሳትዘጋጅ እንደማትቀር ተነገረ።
የጀርመኑ ጋዜጣ ዴር ስፔግል ያወጣቸው የሳተላይት ምስሎች ሩስያ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖቿን በዩክሬን ድንበር ማከማቸቷን ያሳያሉ።
ከዩክሬን ድንበር በ500 ማይል ርቀት ላይ የሚገኘው የአውሮፕላን ማረፊያ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ እንቅስቃሴ በዝቶበታል።
የአውሮፕላኖቹ በርከት ብለው መታየትም ሞስኮ ለአዲስ ዘመቻ መዘጋጀቷን እንደሚያሳይ ነው የወታደራዊ ጉዳዮች ተንታኞች ነገሩኝ ብሎ ዴር ስፔግል የዘገበው።
ተንታኞቹ ኬቭ ምናልባትም በቅርቡ ለመጠነ ሰፊ የአየር ድብደባዎች ተጋላጭ ትሆናለች ማለታቸውን ጋዜጣው አስነብቧል።
አርዳ መቭሉቶግሉ የተባሉ የወታደራዊ ጉዳዮች ምሁር ግን አውሮፕላኖቹ ሚሳኤሎችን ሳያራግፉ እንዳልቀሩ በመጥቀስ የአየር ድብደባው ጉዳይ ብዙም አሳሳቢ አይመስለኝም ነው ያሉት።
የጦር አውሮፕላኖች በርከት ብለው መታየት ወታደራዊ ዘመቻው መጠናከሩን እንደሚያሳይ ግን ገልጸዋል።
ሩስያ ከኬርስን ለቃ ከወጣች ከቀናት በኋላ ዳግም ራሷን አዘጋጅታ አዲስ ዘመቻ መክፈቷ እንደማይቀር ሲነገር ሰንብቷል።
የአሁኑን የሳተላይት ምስልም ከዚሁ ዝግጅት ጋር ያገናኙት ተንታኞች የዩክሬን መሰረተ ልማቶች የተጋረጠባቸውን አደጋ እያነሱ ስጋታቸውን አጋርተዋል።
ሚሊየኖች አሁንም በጨለማ ውስጥ በሚገኙባት ሀገር ሞስኮ በድንበር ዙሪያ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖቿን ማስፈሯም ከባድ ውድመትን ይዞ እንደሚመጣም ግምታቸውን እየገለጹ ነው።
“ሩስያ አውሮፕላኖቿን በስፋት እየጠገነች ነው፤ የምድር ጦሯንም እያንቅሳቅሰች ትገኛለች፤ እናም ሩስያ ለአዲስ ዘመቻ ዝግጁ ሆናለች” ብለዋል ኮናርድ ሙዝይካ የተባሉ የወታደራዊ ጉዳዮች ባለሙያ።
የሳተላይት ምስሎቹ 13 አውሮፕላኖችን ብቻ ያሳይ እንጂ ክሩዝ ሚሳኤል የሚያመላልሱ ተሽከርካሪዎችም እንደሚታዩ ባለሙያው ተናግረዋል።
ከሞስኮ በኩል ዴር ስፔግል ጋዜጣ ስላጋራው የሳተላይት ምስል የተባለ ነገር የለም።