ዩክሬን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ 18 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አግኝታለች
ዩክሬንን መልሶ ለመገንባት 350 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት ከገቡ 10 ወር ሊሞላው ጥቂት ቀናት ቀርተውታል።
በነዚህ የጦርነት ጊዜ ውስጥ ከ15 ሚሊየን በላይ ዩክሬናዊያን ሲሰደዱ በ10 ሺህ የሚቆጠሩት ደግሞ ህይወታቸው እንዳለፈ የተመድ ሪፖርት ያስረዳል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሩሲያ የዩክሬንን መሰረተ ልማት ኢላማ ያደረገ የሚሳኤል ጥቃት በማድረግ ላይ ስትሆን ዋና ከተማዋን ኬቪን ጨምሮ በርካታ የዩክሬን ከተሞች የመብራት እና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች ተቋርጠዋል።
- ሩሲያ በዩክሬን ላደረሰችው ጉዳት 600 ቢሊዮን ዩሮ ካሳ መክፈል እንዳለባት የአውሮፓ ህብረት ገለጸ
- ዩክሬን በኃይል እጥረት ምክንያት ዜጎቿ እንዲሰደዱ ምክረ ሀሳብ አቀረበች
የዓለም ባንክ ባወጣው ሪፖርት በዚህ ጦርነት ውድመት የደረሰባት ዩክሬን መሰረተ ልማቶቿን ዳግም ወደ ስራ ለማስገባት 350 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ ገልጿል።
የባንኩ ፕሬዝዳንት ዳቪድ ማልፓስ እንዳሉት የዩክሬን ገቢ ማስገኛ እና የሕዝብ መገልገያ መሰረተ ልማቶች በጦርነቱ ክፉኛ ተጎድተዋል ብለዋል።
ጦርነቱ አሁንም እንደቀጠለ መሆኑ በአገልግሎት ላይ ያሉት ሌሎች መሰረተ ልማቶች ጥቃት የሚደርስባቸው ከሆነ ለመልሶ ግንባታ የሚያስፈልገው ገንዘብ ሊጨምር እንደሚችልም ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል።
ዩክሬን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ብቻ 18 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ከአሜሪካ እና ከሌሎች አካላት ድጋፍ ማግኘቷን የባንኩ መረጃ ያስረዳል።
አሜሪካ እና አውሮፓ የሩሲያ መንግስት እና ባለሀብቶች ንብረት የሆኑ ከፍተኛ ንብረቶችን ያገዱ ሲሆን ለዩክሬን መልሶ ማገገሚያ እንዲውሉ ግፊት በማድረግ ላይ እንደሆኑ አሳውቀዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ የዩክሬን ጦርነት እንዲያበቃ ከሩሲያ አቻቸው ጋር ለመወያየት እንደሚፈልጉ ተናግረው ነበር።
ሩሲያ በበኩሏ በዩክሬን ጉዳይ ለመነጋገር ዝግጁ መሆኗን አሳውቃ በዩክሬን ያለው የሩሲያ ጦር እንዲለቅ በቅድመ ሁኔታነት በአሜሪካ የቀረበውን ሀሳብ ግን እንደማትቀበል ገልጻለች።