የሩሲያ ጦር በሰሜን ምስራቅ ዩክሬን የሚገኙ 5 መንደሮቸን ተቆጣጠረ
እንደ አዲስ ያገረሸውን የሩሲያ ጥቃት ተከትሎ በርካታ ዩከሬናውያን ከመኖሪያቸው ለመልቀቅ ተገደዋል
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ የዩክሬን ጦር የመልሶ ማጥቃት እርምጃ እየወሰደ ነው ብለዋል
የሩሲያ ጦር በሰሜን ምስራቅ ዩክሬን ውስጥ በአዲስ መልክ እያረገ ባለው ጥቃት አምስት መንደሮችን መያዙን የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የዩክሬን ባለስልጣናት በዩክሬን ካርኪቭ ክልል እና ሩሲያ ድንበር ላይ በሚገኙት "ግራጫ ዞን" ውስጥ የሚገኙትን መንደሮች በሩሲያ እጅ ስለመውደቃወቸው እስካሁን ያሉት ነገር የለም።
የዩክሬን ጋዜጠኞች እንደዘገቡት ከሆነ ግን ቦሪሲቭካ፣ ኦሂርቴሴቭ፣ ፒሊና እና ስትሪሌቻ የተባሉ መንደሮች ባሳለፍነው አርብ በሩሲያ ወታደሮች እጅ ወድቀዋል።
ሩሲያ የፕሌቴኒቭካ የተባለች መንደርም በጦሯ ቁጥጥር ስር መሆኗን አስታውቃለች።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ ትናንት ምሽት በሰጡት መግለጫ፤ በስትሪሌቻ እና ፕሌቴኒቭካ እንዲሁም በክራስኔ፣ ሞሮኮቬትስ፣ ኦሊኒኮቭ፣ ሉኪንቺ እና ሃቲሽቼ በተባሉ መንደሮች ውስጥ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንደቀጠለ ነው ብለዋል።
“ወታደሮቻችን በጦር ግንባሮቹ የዩክሬናውያንን ድንብር ለማስጠበቅ የመልሶ ማጥቃት እርምጃ እየወሰዱ ነው” ብለዋል ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ።
እንደ አዲስ ያገረሸውን የሩሲያ ጥቃት ተከትሎ በርካታ ዩከሬናውያን ከመኖሪያቸው ለመልቀቅ መገደዳቸውም ነው የተነገረው።
የዩክሬን ባለስልጣናት እንደተናገሩት በክልሉ ያገረሸው ጥቃት ከ1 ሺህ 700 በላይ የዩክሬን ዜጎች በግጭቱ አቅራቢያ ካሉ ሰፈሮች ውስጥ ለቀው ለመውጣት ተገደዋል።
ሩሲያ በትናንትናው እለት ቮቭቻንስክ የተባለች መንደርን በአየር እና በሮኬት መደብደቧ የቀጠለች ሲሆን፤ ፖሊሶች እና በጎ ፍቃደኞች ነዋሪዎችን ለማስወጣት ሲሯሯጡ ታተዋል።
ሩሲያ ካሳለፍነው የካቲት ወር ወዲህ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምትሰነዝረውን ጥቃት አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን፤ ዩክሬን በበኩሏ የምእራባውያ የጦር መሳሪያ ድጋፍ በወቅቱ አለመደረሱ ሩሲያ በጦር ግንባር የበላይ እንድትሆን እያደረጋት ነው ብላለች።
የዩክሬን ጦር ዋና አዛዥ ጄነራል ኦሌክሳንደር ሰርሰይኪ ከሳምንት በፊት በጦር ግንባር ያለው ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን መግለጻቸው ይታወሳል።
ዩክሬን ቁልፍ ወታደራዊ ስፍራዎችን ማጣቷን ያመኑት ዋና አዛዡ፤ ሞስኮ በአንዳንድ ስፍራዎች ላይ ታክቲካዊ ስኬትን አስመዝግባለች ብለዋል።
ጄነራል ኦሌክሳንደር ሰርሰይኪ አክለውም ዩክሬን ጦር የሚያስፈለግውን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ከአሜሪካ ከማግኘቱ በፊት ሩሲያ ያላትን የወታደርና የጦር መሳሪያ ቁጥር ብላጫ በመጠቀም ቦታዎችን እየተቆጣጠረች መሆኑንአስታውቀዋል።
አሜሪካ ባሳለፍነው ሳምንት ለዩክሬን የ61 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ያለው ወታደራዊ ድጋፍ ለማቅረብ መወሰኗ ይታወቃል።