ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን አዲስ የጦር ግንባር ከፈተች
ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን በከፊል የያዘቻቸውን አራት ግዛት ለመጠቅለል ጥቃቷን አጠናክራ በመቀጠል በርካታ መንደሮችን እያስለቀቀች ነው
የሩሲያ ኃይሎች በዩክሬኗ የሰሜን ምስራቅ ካርኪቭ ግዛት ላይ ጥቃት በመክፈት አንድ ኪሎሜትር መግፋታቸውን ገልጿል
ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን ካርኪቭ አዲስ የውጊያ ግንባር ከፍታለች።
የሩሲያ ኃይሎች በዛሬው እለት በዩክሬኗ የሰሜን ምስራቅ ካርኪቭ ግዛት ጥቃት በመክፈት በድንበር ከተማዋ ቮቭቻንስክ አቅራቢያ አንድ ኪሎሜቶር በመግፋት ከጦር እንቅስቃሴ ነጻ ቀጣና ለፍጠር መጣራቸውን የዩክሬን ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስጣን ገልጸዋል።
ጥቃቱ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ሙሉ ጦርነት ካወጀች ወዲህ አዲስ ግንበር ፈጥሯል።
ውጊያው በድንበር አቅራቢያ ባሉ የካርኪቭ ግዛቶች አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን ኪቭ ጥቃቱን ለመቀልበስ ተጨማሪ ኃይል ወደ ቦታው መላኳን መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
"ከጠዋቱ አምስት ሰአት አካባቢ የሩሲያ ኃይሎች ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም ምሽጋችንን ለመስበር ሞክረው ነበር" ብሏል ሚኒስቴሩ።
ሮይተርስ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገን የዩክሬን ወታደራዊ ምንጭ ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ የሩሲያ ኃይሎች ወደ ዩክሬን ግዛት አንድ ኪሎሜትር ዘልቀው መግባታቸውን እና አስከ 10 ኪሎሜትር ድረስ የመግፋት አላማ እንደነበራቸው ገልጿል። የኪቭ ጦር ግስጋሴያቸውን ለመግታት ሞክሯል ተብሏል።
የዩክሬን ኃይሎች፣ በጦርነቱ የመጀመሪያው አመት የሩሲያ ኃይሎችን ከአብዛኛው የካርኪብ ግዛት ማስወጣት ችለው ነበር። ነገርግን ባለፈው አመት የሩሲያ ኃይሎች የኪቭን መልሶ ማጥቃት ዘመቻ ካዳከሙ በኋላ ቀስበቀስ ወደ ማጥቃት በመሸጋገር በዶኔስክ ግዛት በደቡብ በኩል እየገፉ ይገኛሉ።
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ባለፈው መጋቢት ወር ሩሲያን ለመከላከል በዩክሬን ግዛት ውስጥ ከጦር እንቅስቃሴ ነጻ ቀጣና ወይም በፈር ዞን ማቋቋም እንደሚፈልጉ ከተናገሩ በኋላ በካርኪቭ ግዛት ፍርሀት ተፈጥሯል። ከእዚያ ወዲህ ለሩሲያ ባላት ቅርብ ምክንያት ለጥቃት ተጋላጭ የሆነችው ካርኪቭ ከባድ የአየር ጥቃት ደርሶባታል፤ የኃይል መሰረተልማቷም ወድሟል።
ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን በከፊል የያዘቻቸውን አራት ግዛቶች ለመጠቅለል ጥቃቷን አጠናክራ በመቀጠል በርካታ መንደሮችን እያስለቀቀች ነው።