በጦር ግንባር ያለው ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን ዩክሬን አስታወቀች
ዩክሬን “ሩሲያ የወታደርና የጦር መሳሪያ ቁጥር ብላጫ በመጠቀም በርካታ ስፍራዎችን እያየዘች ነው” ብላለች
የዩክሬን ጦር ከምስራቃዊ ዶኔስክ አከባቢ ለቀው እየወጡ መሆኑን የሀገሪቱ ጦር ዋና አዛዥ አስታውቀዋል
የሩሲያ ጦር ጥቃት መጨመሩን ተከትሎ በጦር ግንባሮች ያለው ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን የዩክሬን ጦር አዛዥ አስታወቁ።
የዩክሬን ጦር ዋና አዛዥ ጄነራል ኦሌክሳንደር ሰርሰይኪ እንዳስታወቁት፤ የዩክሬን ጦር ከምስራቃዊ ዶኔስክ አከባቢ ለቀው እየወጡ በመውጣት ላይ ይገኛሉ።
ጄነራል ኦሌክሳንደር ሰርሰይኪ በቴሌግራም ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ በጦር ግንባር ያለው ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን አስታውቀዋል።
የዩክሬን ጦር ከምስራቃዊ ዶኔስክ አከባቢ ለቀው እየወጡ መሆኑን ያረጋገጡት ዋና አዛዡ፤ አሁን ላይ ውጊያ እየተካሄደ ያለው ቻሲቭ ያር በተባለ ስፍራ መሆኑንም ገልጸዋል።
አሁነ ውጊያ እየተካሄደ ያለበት ቻሲቭ ያር የኪቭ መንግስት ጠንካራ ይዞታ ሲሆን፤ ሩሲያ አድቪካን ከተቆጣጠረች በኋላ ቻሲቭ ያርን ለመቆጣጠር እየተዋጋች ትገኛለች።
ዩክሬን ቁልፍ ወታደራዊ ስፍራዎችን ማጣቷን ያመኑት ዋና አዛዡ፤ ሞስኮ በአንዳንድ ስፍራዎች ላይ ታክቲካዊ ስኬትን አስመዝግባለች ብለዋል።
ጄነራል ኦሌክሳንደር ሰርሰይኪ አክለውም ዩክሬን ጦር የሚያስፈለግውን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ከአሜሪካ ከማግኘቱ በፊት ሩሲያ ያላትን የወታደርና የጦር መሳሪያ ቁጥር ብላጫ በመጠቀም ቦታዎችን እየተቆጣጠረች መሆኑንአስታውቀዋል።
አሜሪካ ባሳለፍነው ሳምንት ለዩክሬን የ61 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ያለው ወታደራዊ ድጋፍ ለማቅረብ መወሰኗ ይታወቃል።
ሆኖም ግን የአሜሪካ ወታደራዊ ድጋፎች የዩክሬን ወታደሮች በጦር መሳሪያ እጥረት እየተቸገሩ ያሉበት የጦር ግንባሮች ለመድረስ ገና ጊዜ ይወስድባቸዋል ነው የተባለው።
አሜሪካ ባሳለፍነው አርብ ዘመናዊውን የሚሳኤልና አውሮፕላን መቃወሚያ (ፓትሪዮት ሚሳኤል ስርአት) ወደ ዩክሬን ለመላክ ወስናለች።
የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ሊዩድ ኦስቲን እንዳስታወቁት፥ ለፓትሪዮት ሚሳኤል ስርአቱን ጨምሮ 6 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችና ተተኳሾች ወደ ኬቭ በፍጥነት ይላካሉ።
አሜሪካ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ቢሊየን ዶላሮች የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎችን ለኬቭ ብትልክም የተፈለገው ውጤት በአጭር ጊዜ ሊመጣ አልቻለም።
ኬቭ ባለፈው አመት እጀምረዋለው ያለችው ግዛቶቿን የማስመለስ መልሶ ማጥቃትም ከጅምሩ መሰናከሉ አይዘነጋም።