የትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ ግብረ ኃይል ከዛሬ ጀምሮ በጄኔራል ዮሐንስ ይመራል ተባለ
በክልሉ ለ3 ነጥብ 8 ሚሊዬን ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፎችን ለማድረስ ተችሏል ተብሏል
ግብረ ኃይሉ በጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ ነበር ሲመራ የነበረው
የጥቅምት 24ቱን ጥቃት ተከትሎ በትግራይ ክልል የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ ግብረኃይል በጄነራል ዮሐንስ ገብረመስቀል ተስፋ ማርያም እንደሚመራ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
ጽህፈት ቤቱ በክልሉ ያለውን የሰብዓዊ ድጋፍ እና የመሰረተ ልማት ሁኔታ አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል፡፡
ህወሓት በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመውን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ 21ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን ያደረገው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ የሚመራ የአስቸኳይ ጊዜ ግብረኃይል ማቋቋሙን ያስታወሰው መግለጫው ግብረ ኃይሉ ከዛሬ ከየካቲት 24 2013 ዓ/ም ጀምሮ በጄነራል ዮሐንስ ገብረመስቀል ተስፋ ማርያም መመራት እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡
ይህንንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በይፋዊ የማህበራዊ ገጾቻቸው አስታውቀዋል፡፡
“ከዛሬ ጀምሮ የአስቸኳይ ጊዜ ግብረ ኃይሉ በጄኔራል ዮሐንስ ገብረ መስቀል ተስፋ ማርያም አመራር በመታገዝ የማረጋጋት እና መልሶ የመገንባት ሥራውን ይቀጥላል” ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሰፈሩት፡፡
በጽህፈት ቤቱ የወጣው ባለ 4 ገጽ መግለጫ በክልሉ ቅድሚያ በመስጠት ሰብዓዊ ድጋፎችን ለማድረስ እየተደረጉ ስላሉ ጥረቶች አትቷል፡፡
መንግስት በ1 ነጥብ 87 ቢሊዮን ብር ወጪ በክልሉ የሚገኙ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉም ነው በመግለጫው የተጠቆመው፡፡
የውኃ መስመሮችን ለመጠገን 31 ሚሊዮን ብር በመመደብ እየተሰራ መሆኑ የተገለጸም ሲሆን አግልግሎቱ በተቋረጠባቸው አካባቢዎች ውኃ በቦቴ ለማቅረብ እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡
199 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው መድሀኒቶች መቅረባቸውን ያስታወሰው መግለጫው 20 ሆስፒታሎች እና 71 የጤና ተቋማት ስራ መጀመራቸውንም አስታውቋል፡፡
መግለጫው ት/ቤቶችን ለመጠገንና አስፈላጊ ግብዓቶችን ለማሟላት የሚያስችል ከ96 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ ትምህርት ለማስጀመር ዝግጅቱ መጠናቀቁን ገልጿል፡፡
ዛሬ ከመንግስታቱ ድርጅት ኤጄንሲዎች እና ዓለም አቀፍ ረጂ ተቋማትጋር በተደረገው ምክክር ተቋማቱ ለሰላም ሚኒስቴር ብቻ በማሳወቅ ያለምንም ፈቃድ በራሳቸው ኃላፊነት ብቻ እንዲንቀሳቀሱ ስምምነት ላይ ተደርሷል ብሏል መግለጫው፡፡
ሆኖም ግን ይህንን ሽፋን በማድረግ ከሀገሪቱ ሕግ ውጭ የሚንቀሳቀሱ የትኞቹም አካላት በሕግ እንደሚጠየቁ ነው የጠቆመው፡፡
መንግስት የማይካድራውን ጨምሮ አሉ የተባሉ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እየመረመረ እንደሚገኝም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡ ለዚህም በክልሉ የተሰማራው የፌዴራል ፖሊስና የጠቅላይ አቃቤ ሕግ መርማሪ ቡድን አክሱምን ጨምሮ በሌሎቹም የክልሉ አካባቢዎች ምርመራ እያደረገ ነው ተብሏል፡፡
ህወሃት 195 ኪሎ ሜትር የሚሆን የመንገድ መሰረተ ልማት እንዲበላሽ ማድረጉን የገለጸው መግለጫው ይህንንም ለመጠገን 11 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል ብሏል፡፡