የሰብዓዊ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ያለገደብ እንዲንቀሳቀሱ ፈቃድ መሰጠቱን መንግስት አስታወቀ
መንግስት ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በክልሉ ያለውን ሁኔታ እንዲዘግቡ መፍቀዱ ይታወሳል
በትግራይ ክልል የወንጀል ምርመራ በማድረግ ረገድ ለዓለም አቀፍ የቴክኒክ ድጋፍ መንግስት ዝግጁ መሆኑ ተገልጿል
የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ድጋፍ ለማድረግ ያለገደብ እንዲንቀሳቀሱ መፈቀዱን የኢትዮጵያ መንግስት ይፋ አድርጓል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በሰጠው መግለጫ “የሕወሓትን የወንጀል ድርጊት” ተከትሎ በለፉት ወራት ውስጥ የክልሉን ውስብስብ የጸጥታ ሁኔታ፣ ሰብአዊና ማህበራዊ ተግዳሮቶችን ለመፍታት መንግስት የተለያዩ እርምጃዎች መውሰዱን አስታውቋል፡፡ የሰብዓዊ ድጋፍ ድርጅቶችም አሁን ላይ በክልሉ ያለገደብ በመንቀሳቀስ የተራድኦ ስራቸውን ማከናወን እንደሚችሉ ነው ጽ/ቤቱ የገለጸው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ክልሉን ለማረጋጋትና ዜጎች ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱ ለማድረግ እንዲሁም በክልሉ አሁንም ሆነ በቀጣይነት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች አስፈላጊውን ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ ከሰብአዊ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶችና የልማት አጋሮች ጋር በትብብር እንደሚሰራም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አክሎ እንዳለው ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በፌዴራል ተቋማቶቹ አማካኝነት ምርመራ በማድረግ በተለያዩ የወንጀል አይነቶች የተሳተፉ ሁሉንም ወንጀለኞች ለፍትሕ ለማቅረቡን ይቀጥላል፡፡ ምርመራ በማድረግ ረገድ ለዓለም አቀፍ የቴክኒክ ድጋፍ መንግስት ዝግጁ መሆኑን በመግለጽ በጋራ ምርመራ ማድረግ ለሚፈልጉ አካላት ጥሪ አቅርቧል፡፡
የኢትዮጵያ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የካቲት 17 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ለ135 ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድርጅቶች ትግራይ ክልል ገብተው የሰብአዊ ድጋፍ ሂደቱን እንዲያግዙ ፈቃድ መሰጠቱን አስታውቋል፡፡ ለ3.1 ሚሊዮን ዜጎች እስካሁን ድጋፍ መደረጉንም ያስታወቀው ጽ/ቤቱ በክልሉ ያለውን ሁኔታ እንዲዘግቡ ለተለያዩ ዓለማቀፍ ሚዲያዎች ፈቃድ መሰጠቱንም ገልጿል፡፡