የሀውቲ ታጣቃዎች ቴል አቪቭን ያጠቁት በኢራን ሰራሽ ድሮን መሆኑን ጦሩ ገለጸ
ይህ ፍንዳታ የተከሰተው የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ አንድ ከፍተኛ የሄዝቦላ ኮማንደር መግደሉን ካረጋገጠ ከሰአታት በኋላ ነው
የሀውቲ ታጣቂዎች ኃላፊነት በወሰዱበት ጥቃት አንድ ሰው መገደሉን እና ሌሎች አራት ሰዎች መቁሰላቸውን የእስራኤል ጦር እና ድንገተኛ አደጋዎች አገልግሎት አስታውቋል
የእስራኤሏ ቴል አቪቭ ሳማድ-3 በተባለ ኢራን ሰራሽ ድሮን መመታቷን የእስራኤል ጦር ገለጸ።
የሀውቲ ታጣቂዎች ኃላፊነት በወሰዱበት እና በኢራን ሰራሽ ድሮን በማዕከላዊ ቴል አቪቭ በዛሬው እለት በደረሰው ጥቃት አንድ ሰው መገደሉን እና ሌሎች አራት ሰዎች መቁሰላቸውን ጦሩ እና ድንገተኛ አደጋዎች አገልግሎት አስታውቋል።
ይህ ፍንዳታ የተከሰተው የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ አንድ ከፍተኛ የሄዝቦላ ኮማንደር መግደሉን ካረጋገጠ ከሰአታት በኋላ ነው።
የጦሩ ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳኒኤል ሀጋሪ እንደተናገሩት ጦሩ ድሮኑ የተሻሻለ ኢራን ሰራሽ ሳማድ-3 ሞዴል መሆኑን አረጋግጧል።
ቃል አቀባዩ "ግምታችን ከየመን ወደ ቴል አቪቭ እንደተተኮሰ ነው" ሲሉ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
ሀጋሪ የሀማስ ወታደራዊ ክንፍ ኃላፊ ሞሀመድ ዴይፍ በእስራኤል የአየር ጥቃት መገደሉን የሚያሳዩ ምልክቶች እየጨመሩ መሆናቸውን አክለው ገልጸዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በቀጣይ ሳምንት ዋሽንግተንን ለመጎብኘት ከያዙት እቅድ በፊት በቴልአቪቭ ላይ የተቃጣው ጥቃት የጋዛን ጦርነት የበለጠ ያባብሰዋል የሚል ፍርሀትን አሳድሯል።
የእስራኤል ባለስልጣን እንደተናገሩት ድሮኗ ወደ ቴልአቪቭ ስትጠጋ ለምን የማስጠንቀቂያ ደዎሎች እንዳልተሰሙ ለማወቅ ምርመራ እያካሄደ ነው። ቀደም ብለው የወጡ ሪፖርቶች ግን ድሮኗ መታየቷን እና የማስጠንቀቂያ ደወሉ ግን ድምጽ አለማሰማቱን ገልጸው ነበር።
"እያወራን ያለነው ረጅም ረቀት መጓዝ ስለሚችለው ድሮን ነው"ሲሉ ከጥቃቱ በኋላ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የእስራኤል ጦር የአየር ላይ ቅኝት መጨመሩን ነገርግን ንጹሀን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ አለማስተላለፉን ገልጿል።
የቴል አቪቭ ከንቲባ የእስራኤል የኢኮኖሚ መናኸሪያ የሆነችው ቴል አቪቭ አሁን በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ ነች ብለዋል።
እንደሄዝቦላ ሁሉ በኢራን የሚደገፈው የሀውቲ ታጣቂ ቡድን ቃል አቀባይ ቴል አቪቭን በድሮን ማጥቃቱን እና ለሀማስ አጋርነት ለማሳየት ይህን ጥቃቱን እንደሚቀጥል ዝቷል። ቃል አቀባዩ ያህያ ሳርኤ ዋናው ኢላማ " የእኛ ጦር መሳሪያ የሚደርስበት ርቀት ውስጥ ነው" ብሏል።
ቃል አቀባዩ እንዳለው ከሆነ ጥቃቱ የተፈጸመው የመከላከያ ስርአቶችን ጥሶ ማለፍ በሚችለው እና በራዳር በማይታየው "ያፋ" በተባለ ድሮን ነው። "ኦፐሬሽኑ አላማውን መትቷል" ብሏል ሳርኤ።
የእስራኤል-ሀማስ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ከባለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ፣ እስራኤል ለሀማሰ አጋርነታቸውን ካሳዩት የሄዝቦላ እና የሀውቲ ታጣቂዎች ጋር የተኩስ ልውውጥ እያደረገች ነው።
እስራኤል በጋዛ እየወሰደች ባለው መጠነ ሰፊ ጥቃት የሞቱ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ38ሺ በላይ ማለፉን የጋዛ ጤና ሚናስትር መረጃ ያሳያል።