የፓሪስ ክለብ እና ቻይና ኢትዮጵያ አዲስ ብድር እንድታገኝ መፍቀዳቸው ተገለጸ
ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከአይኤምኤፍ እና ዓለም ባንክ 10 ቢሊዮን ዶላር ብድር ለማግኘት ስትደራደር ቆይታለች
ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት ከ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ከብድር እና እርዳታ አግኝታለች
የፓሪስ ክለብ እና ቻይና ኢትዮጵያ አዲስ ብድር እንድታገኝ መፍቀዳቸው ተገለጸ፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ነበር ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይኤምኤፍ ለኢትዮጵያ ሊሰጠው ያሰበውን ብድር እና እርዳታ የከለከለው፡፡
ጦርነቱ እንዲቆም ያደረገው የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት የቆመውን ጨምሮ አዲስ ብድር እንዲሰጣት ለተቋሙ ጥያቄ ያቀረበች ቢሆንም በተደጋጋሚ የተደረጉ ውይይቶች የታሰበውን ያህል ፍሬ ሳያፈሩ ቆይተዋል፡፡
አይኤምኤፍ በድር ለኢትዮጵያ ከመፍቀዱ በፊት 20 አባላት ያሉት ፓሪስ ክለብ በመባል የሚጠራው የበለጸጉ ሀገራት ስብስብ ብድር እንዲሰጥ ይሁንታ እንዲሰጥ ሲጠበቅ ነበር፡፡
የሀገራትን ብድር የመክፈል አቅም በመገምገም ውሳኔ የሚሰጠው ይህ ስብስብ የኢትዮጵያንም አቅም ሲገመግም ቆይቶ ለአይኤምኤፍ ፈቃድ እንደሰጠ ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያና አረብ ኤሜሬትስ በራሳቸው ገንዘብ ለመገበያየት ተስማሙ
ከፓሪስ ክለብ በተጨማሪም ሌላኛዋ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ብድር የሰጠችው ቻይና ኢትዮጵያ ከአይኤምኤፍ ተጨማሪ ብድር እንዲሰጣት ይሁንታቸውንን ሰጥተዋልም ተብሏል፡፡
ብሉምበርግ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የፓሪስ ክለብ አካላትን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው አበዳሪ ሀገራት ለኢትዮጵያ የሰጡትን ብድር ላይ ማስተካከያ ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡
የፓሪስ ክለብ እና ቻይና ስምምነትን ተከትሎ ኢትዮጵያ ከአይኤምኤፍ አዲስ ብድር እንደምታገኝ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ የመንግስታቸውን ዓመታዊ ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ኢትዮጵያ ከአይኤምኤፍ እና ዓለም ባንክ 10 ቢሊዮን ዶላር ብድር ልታገኝ እንደምትችል መናገራቸው ይታወሳል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የተቋማቸውን የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ኢትዮጵያ ከብድር እና እርዳታ 4 ነትብ 5 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን ተናግረው ነበር፡፡
ከተገኘው ገቢ ውስጥም 54 በመቶው ዕርዳታ ነው የተባለ ሲሆን 849 ሚሊዮን ዶላር በብድር የተገኘ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ከተገኘው ገቢ ውስጥም የዓለም ባንክ አንድ ቢሊዮን ዶላር ወደ ኢትዮጵያ ፈሰስ አድርጓል የተባለ ሲሆን ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ጋር መልካም ግንኙነት እንዳላትም ሚኒስትሩ ተናግረው ነበር፡፡